ናይጄሪያ፡- ኮቪድ-19 የግብርና ጉልበት ሠራተኞች ገቢ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ

| December 21, 2020

Download this story

News Brief

ሙርታላ አባስ በናይጄሪያ ካንቶ ግዛት ውስጥ ለ20 አመት ያክል የሩዝ እርሻዎች ላይ በጉልበት ሠራተኛነት ሲያገለግል ኖሯል፡፡ ቦቪድ-19 ምክንያት መንግስት ዜጎች ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ ድረስ በሳምንት ለአምስት ቀናት ቤታቸው እንዲቆዩ አዞ ነበር፡፡ አባስ እና ሌሎች የግብርና ጉልበት ሠራተኞች በሳምንት ለሁለት ቀናት ያህል ለተወሰነ ሰኣት ብቻ ይሠራሉ፡፡ ገቢው አሽቆሎቀለ፡፡ ቤተሰቡ በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ መመገብ ጀመረ፡፡ የኮቪድ-19ን ጫና ለመቋቋምና ወደፊት ሙሉ በሙሉ ከቤት እንዳትወጡ ከተባለ ለመዘጋጀት እንዲረዳው ሙርታላ ገቢ የሚያስገኝለትን የንግድ ሥራ ለመጀመር እያሰበ ነው፡፡

እሁድ ጠዋት ነበር፤ የአየሩ ሙቀት 25 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይሆናል፡፡ ክረምቱ ገብቶ ነበር፡፡ ኮስተር ያለ ፊት ያለው የ40 አመቱ ሙርታላ ትንሽ ራዲዮ እና የሩዝ መፈልፈያ ዱላውን ሳይክሉ ላይ አስሮ ቀስ እያለ ራዲዮውን እያደመጠ ይጋልባል፡፡ ሙርታላ ከቤቱ 10ኪሜ ርቀት ላይ ወደሚገኝ እርሻ ለሥራ እየሄደ ነው፡፡

እንዲህ ይላል፡- “ክረምት ሲገባ እርሻዎች ላይ ሥራ ስለማገኝ እና ቤተሰቤን ለመደገፍ ተጨማሪ ገንዘብ ስለማገኝ ሁል ጊዜ ደስ ይለኛል፡፡ በዚህ ዓመት ግን ኮቪድ-19 ስራየን እና የማገኘውን ገንዘብ ስለቀነሰብኝ ሁኔታዎች ለየት ብለዋል፡፡”

ሙርታላ በናይጄሪያ ካኖ ግዛት በሮጎ አስተዳደር ባሪ አካባቢ የሚኖር የግብርና ሠራተኛ ነው፡፡ ሦስት ሚስቶች እና 13 ልጆች ሲኖሩት ለ20 ዓመት ያክል በሩዝ እርሻዎች ላይ እየተቀጠረ ሰርቷል፡፡

ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ ድረስ መንግስት ዜጎች በሳምንት ለአምስት ቀናት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ማዘዙን ይናገራል፡፡ በዚህም የተነሳ ሙርታላ እና ሌሎች የግብርና ጉልበት ሰራተኞች መስራት የሚችሉት በሳምንት ውስጥ ለሁለት ቀናት ብቻ ነበር፡፡

ገቢው በከፍተኛ መጠን እንደቀነሰበት እና እንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት እንደማያውቅ ይናገራል፡፡ ሙርታላ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡- “ከኮቪድ-19 በፊት በቀን 900 ናይራ (2.32 ዶላር) አገኝ ነበር፤ እንቅስቃሴ ከታገደ በኋላ የቀን ገቢዬ 400 ናይራ (1.03 ዶላር) ብቻ ሆነ፡፡” የቀን ገቢው የቀነሰው በስራ ቀናትም እንኳን ቢሆን በእንቅስቃሴ መታገድ የተነሳ የሚሰራባቸው ሰኣቶች በመቀነሳቸው ነበር፡፡

ቤተሰቡ በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ መመገብ ጀመረ፡፡ ሙርታላ በተጨማሪም እንዲህ ይላል፡- “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ የምግብ ዋጋ ጨመረ፤ መንግስትም ለግብርና ጉልበት ሠራተኞች የሚሰጠው ድጋፍ አልነበረም፡፡”

ሳጊሩ ሮጎ በካ ግዛት ሊማን መንደር ያለ የግብርና ጉልበት ሠራተኛ ነው፡፡ እንቅስቃሴ በመታገዱ የተነሳ የሚያገኘው ሥራ በመቀነሱ የተነሳ ቤተሰቡን በጣም መጎዳቱን እና ምግብ መግዛት አለመቻሉን ይናገራል፡፡

ሳጊሩ እንዲህ ይላል፡- “አስር ልጆች ያሉኝ ሲሆን ኮቪድ-19 ገቢየን ስለቀነሰብኝ ለቤተሰቤ በቀን ሦስት ምግብ ላቀረብ አልችልም፡፡ ለሥራ ወደ እርሻዎች የምሄድበት ሳይክል ነበረኝ፤ ነገር ግን ገቢዬ ስለቀነሰብኝ የቀን ወጭዬን ለመሸፈን ስል ሸጥኩት፡፡”

አክሎም እንዲህ ይላል፡- “በወረርሽኙ እና በእንቅስቃሴ እግዱ የተነሳ የሴት ልጄን ሰርግም ስላስተላለፍኩኝ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት፡፡”

ጁማሎ አዶም ካኖ ግዛት ውስጥ ባሉ እርሻዎች ላይ የምትሠራ ሌላ የጉልበት ሠራተኛ ናት፡፡ መጀመርያ ላይ በኮቪድ-19 አታምን እንደነበር ትናገራለች፤ ራዲዮ ካዳመጠች በኋላ ግን አስተሳሰቧን ቀየረች፡፡ አሁን እጇን በመታጠብ፣ አካላዊ እርቀትን በመጠበቅ እና ሥራ ስትሄድ ማስክ በመጠቀም እራሷን ለመጠበቅ ጥንቃቄ ታደርጋለች፡፡

ጁማሎ የምትሠራባቸው እርሻዎች በኮቪድ-19 ምክንያት የገንዘብ ችግር ስላጋጠማቸው ሠራተኞቹ በገንዘብ ፋንታ ምግብ መቀበል እንደጀመሩ ትናገራለች፡፡

ሙርታላ የእግድ ጊዜው በማብቃቱ ትልቅ እፎይታ እንደተሰማው ይናገራል፡፡ ቤተሰቡን ለመደገፍ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ጠንክሮ እንደሚሠራ ነገር ግን አሁንም ፍርሃት እንዳለበት ይናገራል፡፡ ሲያስረዳም እንዲህ ይላል፡- “የጉልበት ሥራ ሠርቼ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት በጣም እየሞከርኩ ቢሆንም በኮቪድ-19 ምክንያት የኑሮ ውድነት ስለጨመረ የማገኘው ገንዘብ ምግብ እና ሌሎችን ነገሮችን ለመግዛት ይበቃኝ እንደሆነ ገና ወደፊት ነው የማየው፡፡”

የኮቪድ-19ን ጫና ለመቋቋም እና ወደፊት እንቅስቃሴ የታገደ እንደሆነ ለመዘጋጀት ሙርታላ እንደዚህ ባሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት ገቢ ለማግኘት የሚረዳውን የንግድ ሥራ እንደሚጀምር ይናገራል፡፡

ሲያስረዳም እንዲህ ይላል፡- “ወደፊት ለሚፈጠሩ የእንቅስቃሴ እግዶች መጠባበቂያ እንዲሆነኝ ከግብርና ሥራ በተጨማሪ የማገዶ እንጨት እና ከሰል መሸጥ እጀምራለሁ፡፡”

ይህ ጽሁፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡