ቤኒን፡- የሰፈር ብድርና ቁጠባ ማህበራት በኮቪድ-19 ምክንያት እየተቸገሩ ነው

| December 21, 2020

Download this story

News Brief

አንድ ደመናማ እሮብ ቀን በዳንግቦ ቤኒን የምትኖረው ቬሮኒክ አሂሱ የኮሮናቫይረሱ ችግር ሳያንስ ዝናብ ዘንቦ የሰፈሯ የብድርና ቁጠባ ማህበር ስብሰባ አንዳይቀር ፈርታለች፡፡ ማህበሩ ገና ካሁኑ ችግር ላይ ነው፣ አብዛኛዎቹ አበላትም ሳምንታዊ መዋጯቸውን መክፈል አልቻሉም፣ ብድር የመውሰድም አቅም የላቸውም፡፡ ሌላ ጊዜ በቆሎ፣ ሩዝ እና ፐስታ ሽጠው ገቢ የሚያገኙት ሴቶች አሁን በወረርሽኙ ምክንያት ገቢ የማግኘት እቅማቸው ቀንሷል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ስለኮሮናቫረስ መረጃ ስለሚለዋወጡ እና በወረርሽኙ ጊዜም ስለሚረዳዱበት ማህበሩ ለነዚህ ሴቶች አሁንም አስፈላጊ ነው፡፡

ሰኔ መጨረሻ ላይ እሮብ ቀን ጧት አምስት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ሰማዩ ጠቁሮ ዝናብ ጠብ ጠብ ማለት እየጀመረ ነው፡፡ ቬሮኒክ አሂሱ ጠረጴዛዎችን፣ አግዳሚ ወንበሮችን እና ሌሎች ወንበሮችን ከቤቷ ውጭ ካለው ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እያመቻቸች ነው፡፡ “ዛሬ ገበያ ስላልሆነ የማሕበራችን ሴቶች መሰብሰብ ይችላሉ፡፡ ኮሮና ቫይረሱ ላይ ዝናቡ ተጨምሮ ስብሰባችንን እንደማያስቀረው ተስፋ አለኝ” እያለች ነበር፡፡

የ50 ዓመቷ ወይዘሮ ቬሮኒክ ከቤኒን የንግድ ዋና ከተማ 50ኪሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው ዳንግቦ ውስጥ ትኖራለች፡፡ ግቤኖንክፖ የተባለው የሰፈር ብድርና ቁጠባ ማሕበር ፕሬዘዳንት ናት፡፡ ኬር የተባለው አለማቀፍ መያድ ከሚደግፋቸው 2,000 ማሕበራት አንዱ ነው፡፡

የኮሮናቫይረስ ችግር ከጀመረ ወዲህ ከ16ቱ የማሕበሩ አባላት አስሩ ብቻ ስብሰባ መሳተፍ ችለዋል፡፡ የማህበሩ አባላት የሚጠብቅባቸውን የ200 ፍራንክ (0.36 ዶላር) መደበኛ መዋጮ መክፈል አቁመዋል፤ ማሕበሩም ብድር መስጠት አቁሟል፡፡ ለጋራ ፈንድ የሚደረገውን የ50 ፍራንክ (0.09 ዶላር) መዋጮም ለመክፈል እየተቸገሩ ነው፡፡

እነዚህ የሰፈር ብድርና ቁጠባ ማህበራት እንደ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሴፍቲ ኔት ያገለግላሉ፡፡ ሴቶቹ መዋጮ አሰባስበው ለብድር ይጠቀሙበታል፡፡ የተበደሩትን ገንዘብ ለትናንሽ ንግዶች ለመጠቀም ሩዝ፣ ፓስታ፣ በቆሎ እና ሌሎችን ምርቶች በመግዛት መልሰው ይሸጣሉ፡፡ በሚያገኙት ትርፍ መዋጮአቸውን እየከፈሉ ቤተሰባቸውን ይደግፋሉ፡፡

የቡድን ብድሮች ከሶስት ወር በኋላ ከ5% ወርሃዊ ወለድ ጋር ይከፈላሉ፡፡ ወለዱ ሁሉንም አባላት ለመጥቀም የተዘዋዋሪ ብድሩን ሂደት ለመጠበቅ ይጠቅማል፡፡ የጋራ ፈንዱ ደግሞ ችግር ማህበሩ ችግር ላይ የወደቁ አባሎቹን ለመደገፍ ያገለግላል፡፡

የኮሮናቫይረሱ ወረርሽኝ ግን የሴቶችን ገቢ የማግኘት አቅም ቀንሷል፡፡ ወይዘሮ ቬሮኒክ እንዲህ ትላለች፡- “በኮቪድ-19 ምክንያት ከንግድ ስራችን እንደ ከዚህ በፊቱ ገንዘብ አናገኝም፡፡ ስለዚህ የብድሩን መጠን ከ15,000 ፍራንክ (27 ዶላር) ወደ 5,000 ፍራንክ (9 ዶላር) መቀነስ ነበረብን፡፡ ሁሉም ሰው መልሶ መክፈል የሚችለውን ያህል ይወስዳል፡፡ ከችግሩ በፊት ከፍተኛው ብድር 40,000 ፍራንክ (72 ዶላር ነበር)፡፡“

በብድር የሚወጣው ገንዘብ ወደ ትናንሽ ንግድ ሥራዎቹ ይገባል፤ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ግን ሴቶች እዳቸውን ከፍለው እንዳይጨርሱ አድርጓቸዋል፡፡ ቤተሰባቸውን ለመደገፍ እና መዋጮአቸውን ለመክፈል ተጨማሪ ገንዘብ ቢያስፈልጋቸውም  ተጨማሪ ብድር ለመውሰድ ግን ፈርተዋል፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው፡፡

ኤሚሊየን ሁንተን ሚኞንሚዴ የሚባል ሌላ የቁጠባና ብድር ማሕበር ዋና ጸሓፊ ናት፡፡ እንዲህ ትላለች፡- “አርብ እለት የኬር ሰዎች አንዳንድ ጥያቄዎችን ሊጠይቁን መጥተው ነበር፡፡ ከኮቪድ-19 በፊት ችግር እንዳልነበረብን ነገርናቸው፡፡“ አሁን ግን ሁሉ ነገር አስቸጋሪ እንደሆነ እና የማሕበሩ አባላትም ሳምንታዊ ክፍያቸውን መፈጸም እንዳልቻሉ ትናገራለች፡፡

ኬር ማህበራቱን ለመደገፍ አና የኮቪድ-19ን ስርጭት እንዲከላከሉ ለመርዳት ግንኑነቱን ቀጥሏል፡፡ ድረጅቱ ለጓሮ አትክልት እና እንስሳት ለማርባት የሚረዳ ቁሳቁስ ደግፏቸዋል፡፡

ዩዴስ ኡግቤኑ የኬር ቤኒን-ቶጎ ሠራተኛ ናት፡፡ እንዲህ ትላለች፡- “በዚህ ወረርሽኝ በጣም የተጎዱት ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው፡፡ መከላከያ እርምጃዎችንም በተመለከተ ቤተሰቦቻቸውን እና አቻወቻቸውን ለማነቃቃት እነሱ የተሻሉ ናቸው፡፡ ውሳኔ ሰጭነታቸው ይበልጥ ቤት ውስጥ ነው የሚታወቀው፡፡ ባለትዳሮቹ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ምግብ እና ልጆች ማሳደግን በተመለከተ መግባባት አለባቸው፡፡“

እሮብ እለት የዳንገቦው የሚኞሚዴ ማህበር አበላት የሆኑት ሴቶች ማስካቸውን አስተካክለው ወንበራቸውን አራርቀው ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ከኮቪድ-19 ለመከላከል የሚያስፈልጉ መንገዶችን በተራ በተራ ይደግማሉ፡፡ “በመሃላችን አንድ ሜትር እርቀት መኖር አለበት፤ ማስክ መልበስ አለብን፤ እጆቻችንን ቶሎ ቶሎ በውሃ እና በሳሙና መታጠብ አለብን፡፡“ በየሳምንቱ ሲገናኙ ይህንን ማስታወሻ ይደግማሉ፡፡

በዝቅተኛ ወጭ የሚሠራ የእጅ መታጠቢያ የሚያመርቱበት ሥራም ጀምረዋል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲጋረጥባቸው በገቢ ማግኛ እንቅስቃሴዎች ላይ ለማዋል የሰፈር ማህበራቱ የአነስተኛ ብድር ተጠቃሚዎች መሆን ይፈልጋሉ፡፡ የችግሩን ዳፋ ለመቋቋም ብድሩ ይረዳቸዋል፡፡

ይህ ጽሑፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡