ጋና፡- የኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ የወሲብ እና ጾታዊ ጥቃትን ቀስቅሷል

| December 7, 2020

Download this story

News Brief

አቤና ኒዪራ በኮቪድ-19 የተባባሰውን የእናቷን የገንዘብ ችግር ምክንያት ተጠቅሞ እሷ በምትኖርበት የጋና ማሕበረሰብ ውስጥ የሚኖር አንድ ወጣት ወንድ ወሲባዊ ብዝበዛ አድርጎባታል፡፡ ትምህርት ቤት በተዘጋበት ወቅት የ17 አመቷ ወጣት ነፍሰ ጡር ሆነች፡፡ እናቷ አትክልት ገበያ ወስዳ ትሸጣለች፣ የአትክልት ገበያው ግን ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር ሲባል ለሁለት ወር ተዘግቶ ነበር፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጋና እና ሌሎች ሃገሮችም የሴት ልጅ ግርዛት፣ ከ20 ዓመት በታች ያሉ ሴቶች እርግዝና፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማስወረድ እና የሕጻናትን ጋብቻ ጨምሮ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ጨምዋል፡፡

ከሰኣት በኋላ 10 ሰዓት ሆኗል፤ ነፍሰ ጡሯ የ17 ዓመቷ አቤና ኒዪራ ከትምህርት ቤት ተመልሳለች፡፡ የደከማት ትመስላለች፤ በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት ቤት የተዘጋ ጊዜ እንዴት እንዳረገዘች ስትናገር ታለቅሳለች፡፡ አቤና ኒዪራ በኮቪድ-19 የተባባሰውን የእናቷን የገንዘብ ችግር ምክንያት ተጠቅሞ እሷ በምትኖርበት የጋና ማሕበረሰብ ውስጥ የሚኖር አንድ ወጣት ወንድ ባደረሰባት ወሲባዊ ብዝበዛ ምክንያት ነበር ያረገዘችው፡፡ እናቷ አትክልት ገበያ ወስዳ ትሸጣለች፡፡ ነገር ግን መንግስት የአትክልት ገበያውን ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር ሲባል ለሁለት ወር ዘግቶት ነበር፡፡

አቤና እንዲህ ትላለች፡- “ያን ቀን ቤት ውስጥ የሚሠራ ምንም ምግብ አልነበረም፡፡ እናቴ ወደሱ ቤት አብሬው ሄጄ አንድ ከረጢት ሩዝ እንዳመጣ ነገረችኝ፡፡ ገና ቤቱ እንደገባን እኔን እየሳመ ከሱ ጋር ብተኛ ቤተሰባችንን እንደሚንከባከብ ነገረኝ፡፡ እምቢ አልኩት እሱ ግን አስገደደኝና ለማንም እንዳልናገር አስጠነቀቀኝ፡፡”

አቤና በጋና ቦኖ ኢስት ክልል በኪንታምፖ ከእናቷ እና ሦስት እህትና ወንድሞቿ ጋር ትኖራለች፡፡ በመለስተኛ ትምህርት ቤት ሶስተኛ ዓመት ተማሪ ስትሆን በዚህ ዓመት የመሠረታዊ ትምህርት ፈተና ለመውሰድ እየተዘጋጀች ነው፡፡ ነፍሰ ጡር ብትሆንም የመጨረሻዎቹን ፈተናዎች ለመውሰድ እንድትችል ትምህርት ቤት እየሄደች ትምህርቷን እየተከታተለች ነው፡፡

የመጀመርያው ኮቪድ-19 ያለበት ሰው በጋና የተመዘገብ በመጋቢት ወር ነበር፡፡ በበሽታው የሞቱ አንዳንድ ሰዎች ሲኖሩ ለበሽታው ይበልጥ ተገላጭ የሆኑ ብዙ ሰዎች በተለይም ሴቶች እና ልጃገረዶች አሉ፡፡ የእንቅስቃሴ እግዱ እና ሥራ እና ገቢ መቀነስ ያመጡትን ጭንቀት ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ኮቪድ-19 ጾታዊ ጥቃትን አባብሷል፡፡

ማንሳ ዶኩዋ ብቻዋን እንድ ልጅ የምታሳድግ እናት ናት፡፡ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪ ነበረች፣ ነገር ግን የቤት ኪራይ መክፈል እና ምግብ መግዛት በመቸገሯ ለመኖር ስትል ወደ ወሲብ ሥራ ልትገባ እንደነበር ትናገራለች፡፡

“በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሥራዬን አጣሁ፡፡ ለመኖር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፤ ከጭንቀቴ የተነሳ ወደተለያዩ ወንዶች ለመሄድ ልጀምር ነበር፡፡ ሳስበው ግን አግባብ አለመሆኑን ተገነዘብኩ” ብላለች፡፡

በመቀጠልም “የልጄን አባት እንዲረዳኝ ለመጠየቅ ወሰንኩ፡፡ ነገር ግን ለመደገፍ እና ሃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ አልነበረም፡፡ ንግግራችን ወደ ጭቅጭቅ ተቀየረና መታኝ፤ አሁን ጉዳያችን በፖሊስ ተይዟል” ብላለች፡፡

ወይዘሮ ዶኩዋ እንደምትናገረው ኮቪድ-19 ችግር ላይ ባይጥላት ኖሮ ሰውየውን እንዲረዳት አትጠይቀውም ነበር፡፡

ሚካኤል ታጎ በጋና ፕላንድ ፓሬንትሁድ ማሕበር የወጣቶች ፕሮግራም ኦፊሰር ነው፡፡ ኮቪድ-19 የጾታ እና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሯል ይላል፤ በተጨማሪም የሴት ልጅ ግርዛት፣ 20 ዓመት ያልሞላቸው ሴቶች እርግዝና፣ ደህንነቱ ያልተጠበቅ ውርጃ እና የሕጻናት ጋብቻ እንደጨመረ ይናገራል፡፡

አቶ ሚካኤል ታጎ እንዲህ ይላል፡- “በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት ቤቶች ስለተዘጉ እና የእንቅስቃሴ እገዳም ስለተደረገ ጾታዊ ጥቃቶች ጨምረዋል፡፡”

ከእርግዝና እና ልጅ ከወለዱ በኋላ ሴቶች ልጆች ትምህርታቸውን ለመቀጠል ብዙ እና አስጨናቂ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሟቸውም አቤና ግን ትምህርቷን ለመጨረስ ቆርጣለች፡፡ ሀሳቧን እንዲህ በማለት ታብራራለች፡- “ልጄን ከወለድኩ በኋላ ትምህርቴን ለመቀጠል ቃል ገብቻለሁ፡፡ ፈተናው ምንም ይሁን ምን፣ ወጣት እናት በመሆኔ ቢጠቋቆሙብኝም አደርገዋለሁ፡፡ ወደፊት አላማዬን ለማሳካት ስል አደርገዋለሁ፡፡”

ይህ ጽሑፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡