Tesfaye Getnet | July 15, 2021
News Brief
የስንዴ አርሶ አደሩ ቡታ ፈይሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ውል ስምምነት እርሻ ሲነገረው እምብዛም እርግጠኛ አልነበረም። ሆኖም ወንድ ልጁ ከዚህ የአስተራረስ ስምምነት፣ በተለይ በግብይት ስርዓቱ የተሻለ ዋጋ ተጠቃሚ እንደሚሆን አሳመነው። አቶ ቡታ ገበያው ላይ ያለውን ወቅታዊ ዋጋ እከፍላለሁ ካለው የዱቄት አምራች ፋብሪካ ጋር ተስማምቶ ውል ተፈራረመ። ተዋዋይ አርሶ አደሮች በፋብሪካው የሚከማች የስንዴ እህል ካቀረቡ በኋላ፣ አርሶአደሮች በማንኛውም ሰዓት ክፍያ በሚጠይቁ ጊዜ ፋብሪካው ይከፍላቸዋል። ጥቅምት 2013 ዓ.ም፣ አቶ ቡታ ከሶደሬ ዱቄት ፋብሪካ ጋር በተፈራረመው ውል መሰረት 78.9 ቶን ስንዴ አቀረበ። እንደ ሌሎች አርሶ አደሮች ሁሉ፣ አቶ ቡታም ከዱቄት ኩባንያው በማንኛውም ሰአት የእለቱን ዋጋ መሰረት ያደረገ ክፍያ መቀበል ይችላል።
ጊዜው ጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ነበር፣ የጠዋትዋ ጸሃይ ቡታ ፈይሳ ግቢ ውስጥ ብርሃኗን ፈንጥቃለች። ከአቶ ቡታ ግቢ ጀርባ 20 ሄክታር የስንዴ እርሻ እንዲሁም ለከብቶች፣ አህዮችና በጎች ጋጣዎች ይጘኛሉ። የ47 አመቱ አርሶ አደር ከቆርቆሮ ቤቱ ሁኖ በቡድን ያሉ ሰወች ወደ እርሱ ሲያመሩ አየ።
ዕለቱን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፡ “ሰወቹ የመጡት ከዞኑ የግብርና ቢሮ፣ ከስንዴ ዱቄት ፋብሪካዎች እና የመንግስት ካልሆኑ ድርጅቶች ስለ ውል ስምምነት እርሻ እኔን ለማስተማርና በአካባቢያችን ካለው የዱቄት ፋብሪካ ጋር ተዋውዬ ተጠቃሚ እንድሆን ሊያስማሙኝ ነበር።”
አቶ ቡታ በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው እተያ ከተማ፣ ጉቺ ሃቤ ቀበሌ ነዋሪ ነው። እርሱ እንደሚለው መጀመሪያ ላይ፣ የውል ስምምነት እርሻ አስተማማኝ እንዳልሆነ አስቦ ነበር። ምንነቱ እምብዛም የገባው ስላልመሰለው ማሰቢያ ጊዜ እንዲኖረው ሰወቹን በሌላ ጊዜ እንዲመለሱ ጠየቃቸው።
የውል ስምምነት እርሻ ለስንዴ አርሶ አደሮች ምርት ማምረት ከመጀመራቸው በፊት ገቢያ እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር መሆኑን እንዲሁም ፋብሪካው የተወሰነውን የስንዴ እህል እንዲያቀርብ ተስማምተው ውል መፈራረም እንደሚችሉ ለአቶ ቡታ አስረዱት። በምላሹ ደግሞ ፋብሪካው ስንዴውን ያከማቻል፣ ያጓጉዛል እንዲሁም ይገዛል።
የስንዴ ምርቱን ካቀረቡ በኋላ አርሶ አደሮቹ በማንኛውም ሰዓት ገንዘብ ቢጠይቁ ፋብሪካው ይከፍላቸዋል።
ሳምንት ቢያልፈውም አቶ ቡታ የውል ስምምነት እርሻ ላይ ለመሳተፍ ቆራጥ ውሳኔ ላይ አልደረሰም ነበር። በስተመጨረሻ ግን የ24 አመት ወንድ ልጁ እንዲሳተፍ አስማማው።
የሆነውን ሲያስረዳ፡ “ልጄ ባህላዊውን የስንዴ ግብይት ስርዓት ከዘመናዊው ጋር በማወዳደር በፊት ከማገኘው ዝቅተኛ ገቢ መላቀቅ እንደምችል አስማማኝ።” በባህላዊው የግብይት ስርዓት ሻጮች እና ደላሎች ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን በእርሻ ላይ ከሚያወጡት አርሶ አደሮች ይልቅ የበለጠ ገንዘብ ይቀበላሉ ፡፡
ልጁ ካስማማው በኋላ ጥቅምት 2013 ዓ.ም፣ አቶ ቡታ ከሶደሬ ዱቄት ፋብሪካ ጋር በተፈራረመው ውል መሰረት 78.9 ቶን ስንዴ አቀረበ።
እንደ ሌሎች አርሶ አደሮች ሁሉ፣ አቶ ቡታም ከዱቄት ኩባኒያው በማንኛውም ሰዓት በዕለቱ ካለው የገበያ ዋጋ ላይ ተመርኩዞ ክፍያ መቀበል ይችላል። ለዚህም ነው አርሶ አደሮች ገበያ ላይ ያለው ዋጋ ጥሩ እስኪሆን ጠብቀው ወደ ፋብሪካው ክፍያ ለመቀበል የሚሄዱት።
ለምሳሌ፦ ግንቦት 2013 ዓ.ም አቶ ቡታ በ100 ኪሎ ስንዴ 2,200 ብር (51.46 ዶላር) ፋብሪካው እንዲከፍለው ጠይቋል። ኩባንያውም ወድያዉኑ የተጠየቀውን ክፍያ በባንክ ሂሳቡ አስገብቶለታል።
ሲያስረዳ፡ “የስንዴ ምርቴን ለመሸጥ የውል ስምምነት እርሻ ጠቃሚ እንደሆነ አሁን ገብቶኛል… ስለ ዋጋ መለዋወጥ ሳልጨነቅ በፋብሪካው ቀድሞ ከተከማቸው ምርቴ እሸጣለሁ። ምርቴን ለሽያጭ የማቀርበው ገብያው ላይ ያለው ዋጋ ተስማሚ ሲሆን ነው።”
አቶ ቡታ አክሎም “ሁሉም ግብይት የሚከናወነው በባንክ ሂሳብ በኩል ስለሆነ ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ነጻ መሆኑ ለላው ጥቅሙ ነው” ብሏል።
ሰለሞን ተካ የሶደሬ ዱቄት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ነው። “ከአርሶ አደሮች ጋር በውል ስምምነት እርሻ ላይ በሚሰራበት ወቅት ዋነኛው አትኩሮት ሊደረግበት የሚገባው ነገር ተዓማኒነትን መገንባት ላይ ነው። አልፎ አልፎ ውስን የሆኑ አርሶ አደሮችን ለማስማማት ከስድስት ጊዜ በላይ እንሰበሰባለን።”
በአንድ ወቅት ፋብሪካው ከአርሶ አደር ቤት ስንዴ ሊረከብ የመጣ ጊዜ የአርሶ አደሩ ባለቤት በመቃወም ተነስቶ የነበረውን ክርክር ያስታውሳል። “ሚስትየዋ ባሏ እሷ ከምታውቀው ገበያ ውጭ ስንዴውን እየሸጠ መስሏት ነበር። እኛ ግን ማንኛውም ክፍያ ሲደረግ ወዲያው መረጃው እንደሚደርሳት አሳመናት። ከዛ ጊዜ አንስቶ እንደውም የውል ስምምነት እርሻን በአካባቢዋ በማስተዋውቅ ላይ ትገኛለች።”
አቶ ሰለሞን ፋብሪካው በአሁኑ ሰአት ከ1000 በላይ አርሶ አደሮች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራል። አክሎም፡ “በውል ስምምነት እርሻ መሰረት አርሶ አደሮች ተገቢውን የግብርና ልማዶችን በመከተል ጥራት ያለው ምርት ማምረታቸውን በእርሻ ቦታ በመገኘት እንከታተላለን። ምርታቸውንም ወደ ፋብሪካው በማጓጓዝ ድጋፍ እናደርግላቸዋለን። አንዳንዴ ለማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብአቶች ማሟያ እንዲሆን ገንዘብ እናበድራቸዋለን።”
ሸኮ ሻርቴ በአርሲ ዞን የግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ ነው። እርሱ እንደሚለው የውል ስምምነት እርሻ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች የተለመደ እንዳለመሆኑ እምነት መገንባቱ ጊዜ ይፈጃል።
“በአርሲ ከ20,000 በላይ የሆኑ አርሶ አደሮች የውል ስምምነት እርሻን ከአምስት የዱቄት አምራች ፋብሪካዎች ጋር በመሆን እየሞከሩት ነው” ይላል አቶ ሸኮ።
አርሶ አደሮቹ ጥራት ያለው ስንዴ እንዲያመርቱ ለማገዝ ዱቤ፣ ማዳበሪያ እና ትራክተር አቅርቦትን ጨምሮ ጘዢዎች ድጋፍ እየደረጉላቸው እንደሆነም ተናግሯል።
የውል ስምምነት እርሻን በሚመለከት ካለው ተሞክሮ ተነስቶ፣ አቶ ቡታ ሌሎችም የስንዴ አርሶ አደሮች የሱን ፈለግ ተከትለው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያበረታታ ይገኛል። “ጥሩው ነገር ከዚህ ቀደም የውል ስምምነት እርሻ ላይ ያልተስማሙ የስንዴ አርሶ አደሮች ከኔ ተሞክሮ በመነሳት አሰራሩን መከተል መፈለጋቸው ነው” ይላል።
ይህ ስራ የአረንጓዴ ፈጠራ ማዕከልን ፕሮጀክት ለመተግበር ጂ.አይ.ዜድ በሰጠው ድጋፍ አማካኝነት የተዘጋጀ ነው።