ዩጋንዳ፡- ነፍሰ ጡር አናቶች በኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ እግድ የተነሳ የስነ ተዋልዶ አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ ነው

| December 7, 2020

Download this story

News Brief

በዩጋንዳ የተጣለው የኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ እግድ የስነ ተዋልዶ አገልግሎቶችን ተደራሽነት አስቸጋሪ በማድረጉ የተነሳ ነፍሰ ጡር እናቶች በችግር እየተንገላቱ ነው፡፡ የአንድ ልጅ እናት የሆነችው የ25 ዓመቷ ሚሊ አፒዮ ወደ ክልል ሆስፒታል ለመሄድ አቅም ስላልነበራት የዘጠኝ ወር ጽንስ ጠፍቶባታል፡፡ በወረርሽኙ ወቅት የትራንስፖርት ሂሳብ ሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ ወይዘሮ አፒዮ ባጋጠማት የጤና መወሳሰብ ምክንያት ባካባቢዋ ያለው ጤና ጣቢያ 50 ኪሎሜትር እርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደ ጉሉ ክልል ሪፈራል ሆስፒታል ካልሄደች ጽንሱ ሊጠፋ እንደሚችል መክረዋት ነበር፡፡

ሚሊ አፒዮ ወደ ጤና አግልግሎት ማእከል መሄድ ባለመቻሏ የተነሳ ስይወለድ ስለሞተባት ልጇ ስትናገር ታለቅስ ነበር፡፡

በኮቪድ-19 መከላከያ እርምጃዎች ምክንያት ሦስት እጥፍ የጨመረውን የሕዝብ ትራንስፖርት ዋጋ ቤተሰቦቿ መክፈል ባለመቻላቸው ነበር ልጇ የሞተው፡፡ “ያልተወለደው ልጄ፣ የመጀመርያው ወንድ ልጄ ሊሆን የነበረው መሞቱን ማመን አልቻልኩመ” ትላለች፡፡

ወይዘሮ አፒዮ 25 ዓመቷ ሲሆን በጉሉ ዲስትሪክት ኦሮኮ አጥቢያ መንደር ትኖራለች፡፡ አነስተኛ አርሶ አደር ስትሆን ባለቤቷ አካል ጉዳተኛ ነው፡፡

ሃምሌ መጨረሻ ላይ ነበር ያልተወለደው ልጇ በዘጠኝ ወሩ በተፈጠረ መወሳሰብ ምክንያት የሞተባት፤ ሐኪሞች የማህጸን ውስጥ የጽንስ ሞት ይሉታል፡፡

ወይዘሮ አፒዮ ያልተወለደው ልጇ ከመሞቱ አንድ ቀን አስቀድሞ በሆዷ ዝቅተኛ ክፍል እና ማህጸኗ ላይ ደጋግሞ ሕመም ይሰማት ነበር፡፡

“ከቤታችን አራት ኪሎሜትር ርቆ ወደ ሚገኘው ወደ ኦሮኮ ቁጥር ሶስት ጤና ጣቢያ ለሕክምና ሄጄ ነበር፡፡ ዶክተሮቹ 50 ኪሎሜትር ርቆ ወደ ሚገኘው ወደ ጉሉ ክልል ሪፈራል ሆስፒታል ባስቸኳይ ሄጄ ካልታየሁ ልጁን ላጣው እንደምችል ነገሩኝ” ትላለች፡፡

የወይዘሮ አፒዮ ቤተሰብ ግን በኮቪድ-19 ምክንያት የጨመረውን የትራንስፖርት ዋጋ ለመክፈል የሚያስችል ገንዘብ ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡

“ወደ ጉሉ ክልል ሪፈራል ሆስፒታል ለመሄድ የሚያስፈልገው የትራስፖርት ዋጋ 60,000 የዩጋንዳ ሺሊንግ (16.06 የአሜሪካ ዶላር) ነው፡፡ ዋጋው በኮቪድ-19 ምክንያት ሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ መንግስትም እያንዳንዱ መኪና በግማሽ መቀመጫ ብቻ ተሳፋሪ መጫን እንዳለበት አስታውቆ ነበር፡፡”

“ገንዘቡን ለማግኘት ለፍተን ነበር ነገር ግን ኮቪድ-19 በፈጠረው ጫና ምክንያት ዝቅተኛው የንግድ ሥራችን ከስሮ ስለነበር አልቻልንም፡፡ ከባለቤቴ ጋር ሆነን ከተማ ከሚኖሩ ዘመዶቻችን እና ጓደኞቻችን እርዳታ ለመጠየቅ ሞክረን ነበር፡፡ ግን እነሱም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የንግድ ሥራቸው ስለከሰረባቸው ገንዘብ እንደሌላቸው ነገሩን፡፡”

በርቀት ወደሚገኘው ሆስፒታል ሄዳ የጤና አገልግሎት የምታገኝበት ዕድል ሲሟጠጥ ወይዘሮ አፒዮ በሚቀጥለው ቀን ወደ ኦሮኮ ቁጥር ሦስት ጤና ጣቢያ በከፍተኛ ሕመም ተመልሳ ሄደች፡፡

የእሷን እና የልጇን ሕይወት ለማትረፍ የጤና ጣቢያው ሰራተኞች ከጉሉ ክልል ሪፈራል ሆስፒታል አምቡላንስ እንዲላክላቸው ጠየቁ፡፡ አምቡላንሱ ግን በጊዜ መድረስ አልቻም ነበር፡፡ መድማት ስትጀምር ለእሷ እንክብካቤ ማድረግ የሚችል ሰው አምቡላንሱ ውስጥ አልነበረም፡፡

“መንገዱ መጥፎ ስለነበር ሕመሜ እንዲበረታ እና ብዙ ደም እንዲፈሰኝ ያደረገኝ መሰለኝ፡፡ አምቡላንሱ ወደሚሄድበት ለመድረስ ሰባት ሰኣት ያህል መጓዝ ነበረበት፤ በጣም ብዙ ደም ፈሶኝ ነበር የሆነ ችግርም ተፈጥሮ እንደነበር ታወቀኝ” ትላለች፡፡

አምቡላንሱ ሆስፒታል ሲደርስ ወይዘሮ አፒዮ ህሊናዋን እየሳተች ነበር፡፡ ነርሶች ወደ ማዋለጃ ክፍል በፍጥነት ወሰዷት፡፡

ዶክቶሮቹ ያልተወለደው ህጻን የሞተው ከፍተኛ በሆነ ደም መፍሰስ እና በጽንስ መጨነቅ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

“ለኔ ከባድ ሁኔታ ነበር ግን በሁሉም ነገር እግዚአብሔር ያለው እንደሚሆን አውቃሁ፡፡ ኮቪድ-19 የእለት እንጀራየን ብቻ ሳይሆን ልጄንም አሳጣኝ” ትላለች፡፡

“ወደ ጤና ተቋም ለመሄድ የትራንስፖርት ችግር ስላለ ብዙ ጊዜ የቅድመ ወሊድ ክትትል አላደርግም ነበር፡፡ ሲያመኝ ሲያመኝ ሁሉም የሚስተካከል እየመሰለኝ ከመድሃኒት ቤት ሕመም ማስታገሻ እየገዛሁ እውጥ ነበር” ትላለች፡፡

የቅድመ ወሊድ ክትትል አስፈላጊ ነው፤ የአለም ጤና ድርጅት ቢያንስ አራት ጊዜ መደረግ አለበት ይላል፡፡

ዶክተር ክሪስቲን አኪዲ ሱዛን የጉሉ ክልል ሪፈራል ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል ሃላፊ ናት፡፡ በመጋቢት ወር ላይ መንግስት በኮቪድ-19 ምክንያት የእንቅስቃሴ እግድ በሃገሪቱ ዙርያ ካወጀ ወዲህ በጉሉ ክልል ሪፈራል ሆስፒታል በሳምንት ቢየንስ 16 የማህጸን ውስጥ ሞት እና ሞተው የሚወለዱ ሕጻናት ይመዘገባሉ፡፡

ዶክተር አኪዲ እንዲህ ይላሉ፡- “በኮቪድ-19 ምክንያት የሕዝብ ትራንስፖርት መታገዱ እና የትራንስፖርት ዋጋም መጨመሩ ነፍሰ ጡር እናቶች እራሳቸውን እንዲያክሙ እና የልምድ አዋላጆችን እርዳታ እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም የነሱን እና ያልተወለዱ ልጆቻቸውን ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቀ አድርጓል፡፡”

ወይዘሮ አፒዮ ያጋጠማትን አይነት ችግር ለማሰስወገድ ወይም ለመቀነስ ሆስፒታሉ ከኮቪድ-19 ግብረ ኃይል ጋር በመተባበር ነፍሰጡር ሴቶችን ለመርዳት የጀመራቸው ስራዎች አሉ ትላለች ዶክተር አኪዲ፡፡

ስታብራራም እንዲህ ትላለች፡- “በተላያዩ ክልሎች በእናቶች ጤና፣ የማህበረሰብ አውትሪች እና ለድንገተኛ የተዘጋጁ ተጠባባቂ አምቡላንሶችን በተመለከተ ሰፊ የሕዝብ ማነቃቃት ሥራ ጀምረናል፡፡ ነፍሶ ጡር እናቶችም  መደበኛ የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ ለማድረግም እየሠራን ነው፡፡”

ይህ ጽሑፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡