ኢትዮጵያ: አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን ለመቆጣጠር አዘግይቶ መዝራትን እና አስቀድሞ መቆጣጠርን ይጠቀማሉ

October 18, 2018
A translation for this article is available in English French

አርሶ አደር ብርሃኑ ገብረሚካኤል መሬቱ የለማ ቢሆንም ቀጣይ የእርሻ ስራው አሁንም ቢሆን ያሳሰበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ከፋ ዞን ውስጥ ቼና በተሰኘች መንደር ውስጥ የሚኖረው የ 35 ዓመቱ አርሶ አደር ብርሃኑ በሁለት ሄክታር መሬቱ ላይ ቦቆሎን ያመርታል፡፡ በቅርቡ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ማሳውን በማጥቃት ለምግብነት እና ለገቢ ምንጭነት በዋናነት የሚጠቀምበትን ምርቱን ተፈታትኖታል፡፡

አርሶ አደር ብርሃኑ የቦቆሎ ሰብሉ ላይ የተከሰተውን የፈጣን ሁሉን አውዳሚው ተምች ወረርሽኝ ለመከላከል አሁንም ትግል ላይ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አምስት የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳድረው አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት ተምቹ ባደረሰበት ጥቃት የቤተሰቡን የዕለት ፍላጎትና ምግብን እስከ ማሳጣት የደረሰ ችግር አድርሶበታል፡፡

“በየዓመቱ በአንድ ሄክታር እስከ 36 ኩንታል (1762 ኪሎ ግራም) የቦቆሎ ምርት በማምረት በአማካኝ እስከ 288,000 ብር ($10,540 ዶላር አሜሪካ). አገኝ ነበር ፡፡ ሆኖም ግን 2017 በተምቹ ጥቃት የተነሳ ምርቴ ከመጠን በላይ ወርዷል፡፡” ሲልም አርሶ አደሩ ገልጾልናል፡፡

ፈጣን ሁሉን አውዳሚውን ተምች ለመጋፈጥ አርሶ አደር ብርሃኑ እና ሌሎች አርሶ አደሮች ተምቹን ለማስወገድ ይረዳቸው ዘንድ አዘግይቶ መዝራትን እየተገበሩ ናቸው፡፡ ፈጣን ሁሉን አውዳሚው ተምች ጥቃት የሚያደርስባቸውን ከታህሳስ እስከ የካቲት ያሉትን ወቅቶች በማለፍ በሚያዝያ አካባቢ ቦቆሎአቸውን መዝራት ተያይዘዉታል፡፡

“የተምቹን ወረርሽኝ ለማስወገድ አሁን ላይ እየዘራን ነው፡፡ ይህ ወቅት የምንሰበስብበት እንጂ የምንዘራበት ወቅት አልነበረም፡፡ ከታህሳስ እስከ የካቲት ያለው ወቅት ቦቆሎ ለመዝራት ወሳኝ ወቅት ነበር ሆኖም ግን በመጋቢት እና በሚያዝያ ለመዝራት ተገደናል፡፡” ሲልም አርሶ አደሩ ያስረዳል፡፡

ዘብዴዎስ ሰላቶ በኢትዮጵያ ግብርና ሚንስቴር የእንስሳት ሀብት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ተምቹ በኢትዮጵያ መኖሩን ከተረጋገጠበት ከመጋቢት 2017 ጀምሮ የቦቆሎ ሰብሎችን ሲያወድም ቆይቷል፤ ለመለየት እና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

አቶ ሰላቶ አያይዘውም ፈጣን ሁሉም አውዳሚ ተምች ሰፊ ሽፋን ያለው ቦታ ማጥቃት መቻሉ እና በእጅ ለመቆጣጠር አዳጋች መሆኑ አደገኛ ያደርገዋል፡፡ አርሶ አደሮች ተምቹን ለመቆጣጠር የሚያከናውኑት የተጠቁ ሰብሎችን እየለዩ የማስወገድ ስራም ጊዜ ማቃጠል ነው ይላሉ፡፡

አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉም አውዳሚ ተምችን ቀድመው ለመለየት የቻሉትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ የቦቆሎ ማሳቸው በተምቹ በስፋት መጠቃት መጀመሩን ካረጋገጡ ደግሞ በእጃቸው እንዲለቅሙ አልያም ፀረ ተምች እንዲተቀሙ ያሳስባሉ፡፡

አቶ ሰላቶ አያይዘውም መንግስት ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምቹ ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች የግብርና ኤክስተንሽን ባለሙያዎች እየላከ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የግብርና ኤክስተንሽን ባለሙያዎቹ አርሶ አደሮች ተምቹን እንዲለዩ ይረዷቸዋል፤ እንደየ ጉዳቱ መጠንም በእጅ እየለቀሙ በመግደል ወይም ፀረ ተባይ ኬሚካል በማቅረብ ያግዛሉ በማለት ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡

አመንቲ ጫሊ ፊድ ዘ ፊውቸር ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ በተሰኘው ድርጅት የብሔራዊ ሰብል ምርት ባለሙያ ነው፡፡ አመንቲ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች አገር አቀፍ ችግር ሆኗል ፤ ስለዚህም ለመቆጣጠር የሚቻልበት ግንዛቤን የመፍጠር ስራ ደግሞ አንገብጋቢ እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ፊድ ዘ ፊውቸር ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ ከኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሚያ ፣ በደቡብ ፣ በአማራ ፣ እና በትግራይ ክልል ከሚገኙ የሬድዮ ጣብያዎች ጋር በመተባበር ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ለመቆጣጠር በሚቻልበት ዘዴ ዙርያ የሬድዮ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ አመንቲ ቀጥሎም “በ 2018 ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች መከሰቱን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ … በድርቅ የተጎዱ ክልሎችም አሉ፡፡ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ለመቆጣጠርና የቦቆሎ ሰብሎችን ከውድመት ለመታደግ ይቻል ዘንድ የሬድዮ ፕሮግራሞችን ጨምሮ የተለያዩ ግንዛቤን የሚያዳብሩ ስራዎች መሰራት አለባቸው” ብሏል፡፡

አርሶ አደሮች ተምቹን ለመቆጣጠር ተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ሲልም አቶ አመንቲ ምክሩን ይለግሳል፡፡ “ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን የመታገል ስራ የተለያዩ ዘዴዎችን እና ልምዶች ማቀናጀትን ይጠይቃል፡፡ በተለይም ባህላዊ የቁጥጥር ዘዴዎችን ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ፀረ ተባይ፣ ባዮሎጂያዊ ቁጥጥር፣ እና ተምቹን የመቋቋም ብቃት ያለቸው የቦቆሎ ዝርያዎች መጠቀምን ያካተተ የተቀናጀ የተምች ቁጥጥር ስራ መሰራት አለበት” ሲልም አቶ አመንቲ ጨምሮ አስረድቷል፡፡

አቶ አመንቲ ጫሊ አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን የመቆጣጠር ስራ ሲሰሩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከቦቆሎ በተጨማሪ ተምቹ እንደ ሙዝ ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ እና ጤፍ ያሉ ሌሎች ሰብሎችንም ሊያጠቃ ይችላል፡፡

አቶ ብርሃኑ በበኩሉ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች አውዳሚ ጉዳት የሚያደርስ አደገኛ እስከሆነ ድረስ ማሳውን ሁል ጊዜ በመቆጣጠር ተምቹ ሲከሰትም አስቀድሞ ለመለየት እንደሚዘጋጅ ገልፆልናል፡፡

“ባለፈው የምርት ዘመን ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች የቦቆሎ ሰብሌን በከፋ ደረጃ ጎድቶብኛል፤ ለመጪው ወቅት ግን ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ሊያጠቃብኝ የሚችለው በጣም አነስተኛ የማሳዬን ክፍል ብቻ ነው ሚሆነው፡፡ ሰብሎቼን ለመጠበቅ ከመንግስት የግብርና ኤክስተንሽኖች ጋር በመተባበር ፀረ ተባይ ኬሚካል ለመጠቀም ተዘጋጅቼያለሁ፡፡” ሲልም አርሶ አደር ብርሃኑ ገልጧል ፡፡

ይህ ስራ በ ዩ ኤ ስ ኤ አይ ዲ ፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ላይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተደግፎ ለሚዘጋጀው የሬድዮ ፕሮግራም የእገዛ አካል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡