- Barza Wire - https://wire.farmradio.fm -

Uganda፡- የዶሮ አርቢው አርሶ አደር ሕይወት በኮቪድ-19 ምክንያት በተጣለው እገዳ አስቸጋሪ ሆኗል

ከቀኑ ስድስተ ሰዓት ነው፤ ፀሃያማ እና ሞቃት ሲሆን የሙቀት መጠኑ ወደ 30 ዲግሪ ሴልሲየስ እየተጠጋ ነው፡፡ ጀፍሪ ኮማኬች ግን ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የቤት ጣሪያ ክዳን እየከደነ ነው፡፡ አቶ ኮማኬች በሰሜናዊ ኡጋንዳ በጉሉ ዲስትሪክት አዋች ውስጥ በምትገኘው የላትዎንግ መንደር ውስጥ ይኖራል፡፡

የ40 ኣመቱ የዶሮ አርቢ እንዲህ ይላል፡- “አሁን 200 ያህል የሥጋ ዶሮዎች እያሳደኩ ነው፤ እነሱን የመሸጥ እድል አለኝ፡፡” ነገር ግን በኮቪድ-19 ምክንያት የቁም እንስሳት ገበያ ላይ የተጣለው እግድ ነገሮችን ስለቀያየረበት አቶ ኮማኬች ስለገቢው እየተጨነቀ ነው፡፡

“በኮቪድ-19 ምክንያት የቁም እንስሳት ገበያ ላይ በተጣለው እግድ ምክንያት ደምበኞቼ ሁሉ ዶሮ መግዛት አቁመዋል፣ ስለዚህ ገቢዬ ቀንሷል፡፡ ቤተሰቤን የምደግፍበት ገቢ ላይ ተጽእኖ አሳድሮብኛል” ይላልአቶ ኮማኬች፡፡

መጋቢት 13 ቀን የኡጋንዳ መንግስት በዚያ ሰዓት 53 ሰዎችን ይዞ የነበረውን የኮቪድ-19 በሽታን ስርጭት ለመቆጣጠር የሕዝብ ስብሰባዎችን፣ የቁም እንስሳት ገበያዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና የትራንስፖርት ዘርፉን እንደሚያግድ አስታወቀ፡፡ እገዳው ለአንድ ወር ነበር የታወጀው፣ ከዚያ በኋላ ግን ተራዝሟል፡፡ የቁም እንስሳት አሁን መሸጥ የሚችሉት ባደጉበት የእርሻ ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡

በአንጻሩ እስከ ሚያዚያ መጀመርያ ሳምንት ድረስ የምግብ ገበያዎች ክፍት ነበሩ፣ ሻጮች እና ገዢዎች ግን የአራት ሜትር አካላዊ እርቀት እንዲጠብቁ ተጠይቀዋል፡፡ ለድንገተኛ አገልግሎት፣ ለደህንነት አገልግሎት፣ ለጭነት ማመላለሻዎች እና ሌሎች ጥቂት ዘርፎች በቀር የመንግስት እና የግል ትራንስፖርት አገልግሎት በሙሉ ታግዶ ነበር፡፡

እንደ አቶ ኮማኬች ላሉት ዶሮ አርቢዎች የቁም እንስሳት ገበያው መታገድ አስቸጋሪ ነው፡፡ አቶ ኮማኬች አንዲህ ያብራራዋል፡- “ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ከጧት ሁለት ሰአት ጀምሮ ነበር ሥራ የሚበዛብኝ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በሥራ ለማውቃቸው ሰዎች ስልክ በመደወል ቀኔን እጀምር ነበር፡፡”

በመጨመርም እንዲህ ይላል፡- “በየቀኑ ቢያንስ ለደምበኞቼ አስር ዶሮ እያስረከብኩ 100,000 የኡጋንዳ ሽልንግ (26 የአሜሪካ ዶላር) አገኝ ነበር፡፡ ይሄ ገንዘብ ለስድስት ልጆቼ የትምህርት ቤት ወጭ ለመሸፈን ይረዳኝ ነበር፡፡”

የቁም ከብት ገበያው በመታገዱ የተነሳ አቶ ኮማኬች ለደምበኞቹ ዶሮ መሸጥ አይችልም፡፡ ብዙዎቹ ደምበኞቹ ነጋዴዎች ናቸው፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ምንም ዶሮ እየሸጠ አይደለም፡፡

ጥሩ ገቢ ያገኝ እንደነበር እንዲህ ያስረዳል፡- “ለ200 ዶሮዎች ቀለብ በአንድ ወር ከአስር ቀን 1,400,000 የኡጋንዳ ሽልንግ (369 የአሜሪካ ዶላር) አውጥቻለሁ፡፡ ሁሉን ዶሮዎች ከሸጥኩኝ በኋላ በየወር ከአስር ቀኑ 600,000 የኡጋንዳ ሽልንግ (157 የአሜሪካ ዶላር) አተርፍ ነበር፡፡”

ኦባሊም ቻርልስ በጉሉ ዲስትሪክት የእንስሳት ሕክምና ባለስልጣን ነው፡፡ የቁም እንስሳት ገበያው ላይ እግድ ቢኖርም አርሶ አደሮች ከግብርና ቦታቸው ላይ ሆነው ወይም ለደምበኞቻቸው በቀጥታ በማስረከብ መሸጥ ይችላሉ ይላል፡፡ አቶ ቻርልስ ብዙ የቁም እንስሳት ገበያዎች የተጨናነቁና የእጅ መታጠቢያ አቅርቦት የሌላቸው በመሆኑ ለኮቪድ-19 ሊያጋልጡ ይችላሉ ይላል፡፡

ዶ/ር ሩት አሴንግ የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ናቸው፡፡ የቁም እንስሳት ገበያዎችን ማገድ እና ሌሎች ተመሳሳይ እርምጃዎች የኮቪድ-19ን ስርጭ ለመግታት ውጤታማ ናቸው ይላሉ፡፡ ደ/ር አሴንግ አክለውም እንዲህ ይላሉ፡- “እገዳው ባይደረግ ወይም የአካላዊ እርቀት አርምጃዎች ባይወሰዱ ኖሮ ወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጭ ይሆን ነበር፡፡”

ኪያሳኖ ኦላንያ የቁም ከብት አርቢ እና የጉሉ ዲስትሪክት ሉካንዳ ቤቶች ማሕበር ሊቀመንበር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡- “በስጋ ቤቶቻችን ለመሸጥ በቀን እስከ 20 ከብቶች እናርድ ነበር፣ በተጨማሪም ከስድስት እስከ 10 ከብቶችን እንሸጥ ነበር፡፡”

የቁም ከብት ገበያው ላይ እግድ ከተደረገ ጀምሮ አቶ ኦላንያ አሩቅ ሄዶ ለሽያች የሚሆኑት ከብቶች መግዛት ስላልቻለ በአካባቢው ካለ እርሻዎች አየገዛ እንደሆነ ይናገራል፡፡

አቶ ኮማኬች በኮቪድ-19 ዕግድ የተነሳ ወጭውን ለመቀነስ ይሞክራል እንጂ ዶሮ ማርባት እንደማያቆም ይናገራል፡፡ የራሱ የዶሮ መኖ ለማዘጋጀት ያስባል፡፡ በአሁኑ ሰአት ዶሮወቹ ጭረው እየበሉ ስለሆነ ወጭውን ቀንሶለታል፡፡

ይህ ጽሁፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡