- Barza Wire - https://wire.farmradio.fm -

Malawi፡- በኮቪድ-19 የአካላዊ እርቀት እርምጃ ምክንያት ገበያው እና የአርሶ አደሮች ገቢ ተቃዋሷል

ክረምት መው፣ የዕለቱም አየር ቀዝቃዛና ደረቅ ነበር፡፡ ሀዚ ቀን ከቀትር በኋላ አይዳ ማጋንጋ ከቤቷ 200 ሜትር ከሚርቀው የድንች እና ቲማቲም እርሻዋ እተመለሰች ነበር፡፡ የ35 ኣመቷ የሦስት ልጆች እናት ግራ የገባት እና የከፋት ትመስላለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሷን ምርት የሚገዙት ደምበኞች በእሷ አካባቢ ወዳለው ገበያ በብዛት መምጣታቸውን ትተዋል፡፡ 

ወይዘሮ ማጋንጋ ይህ የሆነው መንግስት ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር በወሰደው የአካላዊ እርቀት እርምጃ ነው ትላለች፡፡ ስለዚህ ምርቷን የምትሸጥበት መንገድ ፈጥና መፈለግ አለባት፡፡

 “የኮሮናቫይረስ በሽታ መምጣት ዱሮውንም ረክሶ የነበረውን የድንች እና ቲማቲም ዋጋ የበለጠ ያሽመደምደዋል፡፡ ገቢየን በጣም ነው የሚቀንስብኝ” ትላለች፡፡

የወይዘሮ ማጋንጋ እርሻ በዴድዛ ዲስትሪክት ካፕኑካ መንደር ከዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ 90 ኪሎ ሜትር እርቆ ይገኛል፡፡ ስለ ኮቪድ-19 መጀመርያ የሰማችው በራዲዮ ነበር፤ በኋላ ደግሞ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሞባይሏ የማንቂያ መልክት ደረሳት፡፡

“ኮሮናቫይረስ የያዘው ሰው ምልክቱ ሳል፣ ማስነጠስ እና ትኩሳት እንደሆነ ሰማሁ” ትላለች፡፡ “የፈራሁት ግን መንግስት ብዙ ሰዎች እንዳይታመሙ  በሚል አካላዊ እርቀት ማወጁን ስሰማ ነበር፡፡ አርሶ አደር እንደመሆኔ ይህ ውሳኔ እንደሚጎዳኝ አወቅሁ፡፡”

የማላዊ መንግስት ሰዎች በመካከለቻው ቢያንስ አንድ ሜትር እንዲራራቁ፣ እጅ መጨባበጥ እንዲያቆሙ፣ ከ100 ሰው በላይ እንዳይሰበሰብ እና በግል እና በሕዝብ መኪናዎች ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ ይመክራል፡፡ ሰርግ እና ሐይማኖታዊ አገልግሎቶች ተከልክለዋል፡፡

መንግስት በተጨማሪም ገበያዎች ለግማሽ ቀን ብቻ ክፍት እንዲሆኑ ወስኖ ነበር፣ ግን ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ በመውደቁ ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡ ሰዎች በገበያ ቦታዎች እርቀታቸውን መጠበቅ አለባቸው፣ እያደረጉት ግን አይደለም፡፡

ወይዘሮ ማጋንጋ የኮቪድ-19 ቁጥጥር እርምጃዎች የተነሳ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ የሚወስዱበት መንገድ ተቀይሯል ትላለች፣ ምክንያቱም ለደምበኞች ገበያ ላይ ማቅረብ ማህበራዊ ግንኙነት ይጠይቃል፡፡ “የኮቪድ-19 እርምጃዎች ወደ ገበያ እንዳንደረስ ስላደረጉን ከግብርና የምናገኘው ገቢ ይቀንሳል፡፡ ቤተሰቤን ለመደገፍ ስል የቲማቲም እና ድንች ምርቴን በአካባቢያችን ባለ ገበያ እሸጣለሁ” ትላለች፡፡

ኦሊቨር ኢኖክ ቲማቲም ከአርሶ አደሮች እርሻ እየገዛች ባካባቢው ገበያ ላሉት ነጋዴዎች በሽያጭ ታከፋፍላለች፡፡  የሁለት ልጆች እናት ስትሆን በዴድዛ ዲስትሪክት እንኩንጉምቤ መንደር ትኖራለች፡፡

ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ያሉ አርምጃዎች ሥራዋን እየገደሉባት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ በማሕበራዊ እርቀት ድንጋጌው የተነሳ በአንድ መኪናውስጥ ጥቂት ተጓዦች ብቻ ስለሚፈቀድ ብዙ ነጋዴዎቸ የሷን ቲማቲም እና ድንች ገዝተው ለማጓጓዝ እየተቸገሩ ነው፡፡

አክላም እንዲህ ትላለች፡- “ከበሽታው በፊት ከአርሶ አደሮች አምስት ቅርጫት ቲማቲም እገዛና 5,000 የማላዊ ኳቻ (6.7 የአሜሪካ ዶላር) አተርፍ ነበር፡፡ ማህበራዊ እርቀት ከተደነገገ በኋላ በቀን ሦስት ቅርጫት ብቻ ቲማቲም እገዛና 3,000 የማላዊ ኳቻ (4 የአሜሪካ ዶላር) አተርፋለሁ፡፡”

ሪቻርድ እንጉሉዌ በሊሎንግዌ ገጠራማ ወረዳ በእንቼቼ መንደር የሚኖር የ29 ዓመት የኣሳ ነጋዴ ነው፡፡ የማህበራዊ እርቀት እርምጃዎች የእለት ትርፉን ከ8,000 የማላዊ ኳቻ (10.7 የአሜሪካ ዶላር) ወደ 3,000 የማላዊ ኳቻ (4 የአሜሪካ ዶላር) ቀንሰውበታል፡፡

ሚስተር እንጉሉዌ እንዲህ ያስረዳል፡- “ኮሮናቫይረስ ገዳይ እንደሆነ ይገባኛል፣ ማህበራዊ እርቀቴን ለመጠበቅ እየሞከርኩ ነው፡፡ ግን የአሳ ገበያዬ አልንቀሳቀስ እያለኝ ስለሆነ እርምጃው እለታዊ ሕይወቴ ላይ ተጽእኖ እያሳደረብን ነው፡፡ እምተዳደረው ከሃይቁ በሚወጡ አሶች ነው፤ እነዚህን የኮቪድ-19 እርምጃዎች ከተከተልኩ አሳ ከየት አገኛለሁ፣ ለማንስ እሸጠዋለሁ?”

ቺሶሞ ቦታ በዴድዛ ወረዳ የኤክስቴንሽን ባለሙያ ነው፡፡ እንደ ማህበራዊ እርቀት ያሉ እርምጃዎች የገበያ እንቅስቃሴን በመቀነስ የአርሶ አደሩ ገቢ ላይ ተጽእኖ ቢያሳድሩም ቫይረሱን ለመዋጋት አርሶ አደሮች እነዚህን አርመጃዎች መከተል አለባቸው፡፡

“ሁሉም ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ኦቾሎኒ እና በቆሎ ከገጠር ነው ለከተማዎች የሚቀርበው፡፡ አርሶ አደሮች ለሁሉም ማእከል ስለሆኑ እና ከተማ ለሚኖሩ ሰዎች ዋነኛ የምግብ ምንጭ ስለሆኑ በኮቪድ-19 እንዳይያዙም ሆነ እንዳያስተላልፉ መረጃ ልናደርሳቸው ያስፈልጋል” ይላል አቶ ቦታ፡፡

የወይዘሮ ማጋንጋ ገቢ ቢቀንስም፣ የኑሮ ደረጃዋ ላይም ዘላቂ ጉዳት ቢያመጣባትም ራሷንና በቤተሰቧን ለመጠበቅ ስትል ማሕበራዊ እርቀቷን መጠበቅ እንደምትቀጥል ትናገራለች፡፡

እንዲህ ስትል ታስረዳለች፡- “የዚህ ዓመት እቅዴ ከግብርና የማገኘውን ትርፍ ተጠቅሜ ቤቴን ማደስ ነበር፡፡ አሁን ግን ዋጋ ስለረከሰ ገበያም ስለቀነሰ ትርፌ ይቀንሳል፡፡ ህልሜን ለማሳካት የማህበራዊ እርቀት ውሳኔ ተነስቶ የተሻለ ቀን እስከሚመጣ እጠብቃለሁ፡፡”

ይህ ጽሁፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡