- Barza Wire - https://wire.farmradio.fm -

ኢትዮጵያ : አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን ለመቆጣጠር በእጅ መልቀምን እና የተለያዩ ዘዴዎችን ይተገብራሉ

አለም ደግፌ ከፕላስቲክ የተሰራ ቡትስ ጫማውን አጥልቆ በጭቃማው የቦቆሎ ማሳው ላይ በዝግታ እየተራመደ ነው፡፡ 40 ሴንቲ ሜትር ያህል ብቅ ያሉት የቦቆሎ ሰብሎቹን ቅጠሎች በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች እንዳይጎዱ በአንክሮ ይቃኛል፡፡

የኢትዮጵያ መዲና ከሆነችው ከ አዲስ አበባ በስተምዕራብ በኩል 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአምቦ ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ ድጋፌ በማሳው ምንም ተምች ባለማየቱ ዛሬ በጣም ደስተኛ ሆኗል፡፡

የሶስት ሄክታር ስፋት ያለው የቦቆሎ ማሳውን በዚህ መልኩ በየቀኑ በመጎብኘት ባለፈው ዓመት ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች የበርካታ አርሶ አደሮች የቦቆሎ ማሳ ላይ ያደረሰውን ጥቃት መልሶ እንዳይደገም ጥረት ያደርጋል፡፡

“ስለ ፈጣኑ ሁሉን አውዳሚ ተምች ምንነት እና እንዴት እንከላከለዋለን በሚለው ዙርያ መረጃ አላገኘንም ነበር መረጃውን በደንብ ብናውቀው ኖሮ ተምቹ በማሳዎቻችን ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ መቀነስ እንችል ነበር፡፡” ሲልም ገልፆልናል፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመንግስት የኤክስቴንሽን ሰራተኞች አቶ ድጋፌን ጨምሮ በአካባቢው ላሉት አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚችሉ የሚያስገነዝብ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል አቶ ድጋፌ ተምችን ለመከላከል የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ያስብ ነበር፡፡ ስልጠናውን ከወሰደ በኋላ ግን አውዳሚውን ተምች ለመከላከል ባህላዊ ዘዴዎችን ቀዳሚ ምርጫው አድርጓል፡፡

አቶ ድጋፌ በማያያዝም “ተምቹን በእጅ እየለቀምኩ በምግብነት ለደሮዎቼ እሰጣለሁ፡፡ ኬሚካሎች ለኣካባቢ ጥሩ አይደሉም፡፡” በማለት ያስረዳል፡፡

ሺመልስ አየነው በኢትዮጵያ ሚዛን የዕፅዋት ጥበቃ ማዕከል ውስጥ ተማራማሪ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን ለመቆጣጠር የሚያስችሏቸው ዘዴዎች በመማራቸው ከባለፈው ዓመት የተሻለ አዝመራ ያገኛሉ፡፡

እንደ ሽመልስ አባባል አርሶ አደሮች ማሳዎቻቸውን ገና ሲያዘጋጁ ካለው ጊዜ ጀምረው ተባይ የመቆጣጠር ስራዎቻቸውን መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ በጥልቀት ሲያርሱ መሬት ውስጥ ያሉትን እጮች ለፀሀይ እንዲጋለጡ በማድረግ እንዲሞቱ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሽመልስ አያይዞም ከፀረ ተባይ ኬሚካሎች በተጨማሪ አርሶ አደሮች በእጅ የመልቀምን ፤ እንቆላሎችን እና የሳት ራቶችን ማውደምን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ዘዴዎች መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡

ሽመልስ “በየቀኑ ያለማቋረጥ የሰብሉ ቅጠሎችን እና ግንዶቻቸውን በማየት በሚገባ መከታተል ዕፅዋቶችን ከፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ለመከላከል ወሳኝ ሚና አለው፡፡” ሲልም አብራርቶልናል፡፡

የ 32 ዓመቷ የሺ ዱጋሳ በኦሮሞያ ክልል በቦቆሎ ምርት ከሚታወቁ አካባቢዎች አንዷ በሆነችው በሆሩ ጉድሩ ዞን የምትኖር እና የሶስት ሄክታር የቦቆሎ ማሳ ባለቤት ናት፡፡ የሺ እንደምትለው ባለፈው አመት ማሳዋ የሌሎቹ ያህል በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች አልተጎዳም ነበር፡፡ ምክንያቱም ተምቹን በፍጥት ለይታ በኣካባቢዋ ላሉ የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ለማሳወቅ በመቻልዋ ነው፡፡

በዚህ ዓመት ጉዳዩ ብዙም አያስጨንቃትም ፤ ምክንያቱም በየቀኑ ማሳዋን በመከታተል ላይ በመሆኗ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አረሞች ለተምቾች መደበቂያ ስለሚሆኑ ማሳዋን በማረም ላይ እንደሆነችም ነግራናለች፡፡

የሺ “አረሞች ለፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምቾች እንደ አማራጭ መጠለያ ሆነው ስለሚያገለግሉ ትኩረት ሰጥተን እናርማለን፡፡”

አተ ድጋፌ እንደሚለው ሰብሎችን ከማረም እና ከመከታተል ባለፈ አርሶ አደሮች በማሳዎቻቸው አካባቢ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምቾች በቦቆሎ ምትክ ሊያጠቋቸው የሚችሉ ዕፅዋቶችን መትከል ይኖርባቸዋል፡፡

አቶ ድጋፌ በተጨማሪም ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ላይ በሚያተኩሩ የተለያዩ ዓውደ ጥናቶች ላይ መሳተፉን ገልፆልናል፡፡ ምክንያቱም የቦቆሎ ቤተሶቦቹን የሚያስተዳድርበት የገቢ ምንጩ ስለሆነ ነው፡፡ አቶ ድጋፌ በዚህ ወቅት ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን በመቆጣጠር ዙርያ ያለውን ዕውቀት መሻሻሉን ነው የገለፀልን፡፡

አቶ ድጋፌ በተጨማሪም “የቦቆሎ ሰብሎቼ በተምቹ እንዳይጠቁ በቅርበት መከታተሌን እቀጥልበታለሁ፡፡ ለእኔ ዝቅተኛ አዝመራ ማለት ልጆቼ ትምህርታቸውን በትክክል መከታተል አይችሉም ማለት ነው፡፡ ”

ይህ ስራ በዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ የፕሮጀክቱ አካል በመሆን ባደረገው ድጋፍ የተዘጋጀ ነው፡፡ “ICT-enabled Radio Programming on Fall Armyworm (FAWET).