- Barza Wire - https://wire.farmradio.fm -

ኢትዮጵያ፦ አርሶ አደሮች ዶሮዎቻቸውን በመመገብና በመንከባከብ ያሳዩት ትኩረት የቤተሰብ ገቢያቸውን እያሳደገላቸው ነው

Download the story in Sidamigna [1]

Download the story in Oromifa [2]

ገና ማለዳ ነው፣ አስፎ ዋስ ዶሮዎቹን ለመንከባከብ በሃይል እና በጉጉት ከእንቅልፉ ነቅቷል። የዶሮዎቹን ቤት ጠረገ፣ በቂ ውሃና መኖ ጨመረላቸው። ለሁለት አመት ያህል ዶሮ ያረባ ሲሆን ስድስት ቤተሰብ በሚያሰተዳድርበት በሚያገኘው ገቢም ደስተኛ ነው።

የዶሮዎቹን ጤንነት ለመጠበቅ አቶ ዋስ  እንዴት እና ምን እንደሚመገቡ በጥንቃቄ ይከታተላል። እንዲህ ሲል ያብራራል፦ “ጧት ጧት ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ከመላኬ በፊት ዶሮዎቹ በደምብ መመገባቸውን እና የሚጠጡት በቂ ውሃ መኖሩን አረጋግጣለሁ። በቀን ሦስት ጊዜ የበቆሎ እና ሩዝ ቅልቅል እመግባቸዋለሁ።”

አቶ ዋስ በወር 50 ኪሎ በቆሎ እና 50 ኪሎ ሩዝ ገዝቶ በመቀላቀል ወፍጮ ቤት ወስዶ እስፈጭቶ ለዶሮዎች ምግብነት ያዘጋጃል። አቶ ዋስ እንዲህ ይላል “ባለቤቴ ዶሮዎችን በመመገብ እና ጤናማ ሆነው ለማደግ የጸሃይ ብርሃን ስለሚያስፈልጋቸው ከቤታቸው እንዲወጡ በማድረግ ታግዘኛለቸ።”

አቶ ዋስ አራት ልጆች ያሉት ሲሆን በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በሰሜን ቤንች ወረዳ በያሊ ከተማ ውስጥ ይኖራል። ከዶሮዎቹ የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግ የዶሮ ሥራውን ለማስፋፋት እንደሚፈልግ ይናገራል። ያንን ለማድረግ የላቀው አማራጭ ለዶሮዎቹ ጥሩ መኖ ማቅረብ እና ጤናቸውን መንከባክበ ነው።

አቶ ዋስ ቤተሰቡ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው ከዶሮ እርባታ ሥራ ገቢውን ለማሳደግ የሚያስፈልገው ክህሎት እና እውቀት እንዳለው ያምናል።

ሲያስረዳም እንዲህ ይላል፦ “ባለፉት ሁለት አመታት ጤናማ እና ለገበያ ብቁ የሆኑ ዶሮዎችን በማርባት ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት የሚያስፈልገኝን ክህሎት ተምሪያለሁ። በአካባቢያችን ያሉ የእንስሣ ጤና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ስልጠናዎች ተሳትፊያለሁ፤ አሁንም ስለዶሮ እርባታ ለመማር እነዚህን ስልጠናዎች መውሰድ ቀጥያለሁ።” አቶ ዋስ ስልጠናውን የወሰደው በደቡባዊ ኢትዮጵያ በከፋ ዞን በሚገኘው በቦንጋ ዶሮ እርባታ ነው።

አቶ ዋስ በአሁኑ ሰአት 20 ዶሮዎችን ያረባል። በቅርቡ 20 ተጨማሪ ጫጩቶችን ለመቀበል 300 ብር (7.83 ዶላር) ከፍሏል።

እንዲህ በማለት ያብራራል “ዶሮ ለማርባት የሚሆን በቂ ቦታ አለኝ። በቅርብ ለምቀበላቸው 20 ጫጩቶች ተጨማሪ ቤት ለማዘጋጀት አቅጃለሁ።” አዳዲስ ጫጩቶችን ለመቀበል ቦታውን በጥሩ ሁኔታ ማዘጋጀት የዶሮ በሽታዎችን ለመከላከል በጣም አስፈላጊ ነው።

አቢይ አለማየሁ በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ የግብርና ባለሙያ ነው። ኢትዮ ቺክን ከሚባል መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር ለአርሶ አደሮች የዶሮ እርባታ ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ ይናገራል። አርሶ አደሮቹ አንዴ ዶሮ እርባታ ከጀመሩ በኋላ ስኬታማ ምርት መኖሩን ለማረጋገጥ አሰልጣኞቹ ክትትል ያደርጋሉ።

አቶ ዋስ ከስልጠናው ያገኘው ትልቁ ትምህርት ዶሮዎችን እንዴት ከበሽታ መከላከል እንደሚችል ነው። 

እንዲሀ ይላል፦ “ጫጩቶቹ ለበሽታ ተጋላጭ የሚሆኑባቸው ወቅቶች አሉ፣ ስልጠናው የሚጠቅመው የዚያን ጊዜ ነው። ጫጩቶቹ ሦስት ዙር ክትባት ማግኘት እንዳለባቸው ተምሪያለሁ።”

የታመሙ ዶሮዎች አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ ከእንስሣት ሕክምና ባለሙያዎች ጋር ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በመጨመርም እንዲህ ይላል፦ “ለአርሶ አደር ጓደኞቼ ምሳሌ ለመሆን ተስፋ አደርጋለሁ። እነሱም ከእውቀቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተማርኩትን አካፍላቸዋለሁ።”

አቶ ዋስ የስኬትን ፍሬ መቅመሱን እና የሚያረባቸውን ዶሮዎች ቁጥር በማሳደግ ተጨማሪ ትርፍ ለማግኘት ያለውን እምነት ይገልጻል።

“ባለፈው አመት ስለዶሮ እርባታ የተማርኩትን ትምህርት በመተግበር ብቻ ከ 50,000 ብር በላይ (1,330 ዶላር) ገቢ አግኝቻለሁ። አራት ጊዜ ዶሮ አሳድጌ ሽጫለሁ።” ይላል።

ዶሮ እርባታ ዋነኛ የገቢ ምንጩ እየሆነ ሲሆን ቤተሰቡን በዶሮ እርባታ መደገፍ እንደሚችል እያሰበ ነው። “ከዶሮ እርባታ የማገኘውን ገቢ ተጠቅሜ ልጆቼን ጥሩ ትምህርት ቤት ለማስገባት ወስኛለሁ።” ይላል።

ይህ ጽሑፍ ከአይኤፍሲ በኢትዮጵያ የዶሮ እርባታ ማስፋፋት የራዲዮ ፕሮግራም ለመደገፍ በተሰጠ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጅ።