- Barza Wire - https://wire.farmradio.fm -

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ:- የዱር ስጋ መመገብ መከልከሉ የማሕበረሰቡ አመጋገብ ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል

ከጠዋቱ አንድ ሰኣት ነው፤ በምስራቃዊ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በሚገኘው የቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ ቀለል ያለ ዝናብ እየጣለ ነው፡፡ በአካባቢው የሚኖረው ፓሉሉ ካፖሶሊና ከጎጆው አጠገብ እሳት ለማንደድ ጎንበስ ብሏል፡፡ አቶ ካፖሶሊና 30 ዓመቱ ነው፤ የፊቱ መቋጠር ግን እድሜው ከዚያ በላይ የሆነ ያስመስለዋል፡፡

ይህ ወጣት ምግቡን የሚያገኘው በሕገ ወጥ መንገድ አድኖ ነው፡፡ ነገር ግን ከእንስሳ የሚመጡ እንደ ኢቦላ እና አዲሱ ኮሮናቫይረስ አይነት የቫይረስ በሽታዎች መሰራጨት ሲጀምሩ የዱር ስጋ አድኖ መብላት ተከልክሏል፡፡ መልእክቱ ለሁሉም ሰው በግልጽ እንዲደርስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች ተደርገዋል፡፡ ደን አካባቢ የሚኖሩ ማሕበረሰቦች ግን ለረጅም ጊዜ አብዛኛውን ገምቢ ምግብ የሚያገኙት ከዱር ስጋ ስለሆነ ክልከላውን ለመከተል ተቸግረዋል፡፡

አቶ ካፖሶሊና እንዲህ ይላል፡- “ህልውናየ እዚሁ ነው፡፡ በየቀኑ ሌሊት ከአስራ አንድ ሰኣት በፊት እነሳና ቁጥቋጦ ስር ያጠመድኩትን ወጥመዴን አይቼ የያዘልኝን እንስሳ ይዤ እመጣለሁ … ዛሬ ግን አልሄድም፣ ደምበኞቼም ልክ እንደኔ እየተሰቃዩ ነው፡፡”

ኮቪድ-19 ከመምጣቱ እና የዱር ስጋ መብላት ከመከልከሉ በፊት የአለም ቅርስ ተብሎ እንደተመዘገበው እንደ ቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ የመሳሰሉ ቦታዎች ውስጥ ማደንን የኮንጎ መንግስት በሕግ ከልክሏል፡፡ እንደ አቶ ካፖሶሊና ያሉ አዳኞች ግን በሕገ ወጥ መንገድ መግባት ቀጥለዋል፡፡

ማሌሴ ዪራዪራ የማሕበረሰብ መሪ እና አንትሮፖሎጂስት (የሰው ዘር፣ ባህልና ልማድ አጥኚ) ነው፤ የአደን እግዱ የማህበረሰቡን አመጋብ እና ልማድ አደጋ ላይ ይጥለዋል ብሎ ይሰጋል፡፡ ሁኔታውን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡- “የዱር እንስሳት ማደን ወይም መመገብ የሚከለክለው ሕግ ከቀጠለ ገምቢ ምግባቸውን በዋናነት ከዱር እንስሳት የሚያገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነባር ወይም የገጠር ማሕበረሰቦች የተመጣጠነ ምግብ ያለማግኘት አደጋ ይደቀንባቸዋል፡፡”

በዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎች ዝንጀሮ፣ ቀበሮ፣ የዱር እርግብ፣ የዱር አሳማ፣ አይጥ፣ አጋዘን፣ ጎሽ እና ሌሎችንም የዱር እንስሳት እያደኑ እንደሚኖሩ ይናገራል፡፡ አንዳንዶቹም እነዚህን እንስሳት ከቀደምት አባቶቻቸው ጋር በመንፈስ በመገናኘት የማሕበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት ባላቸው ልማድ ለመስዋእትነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡

በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው ሲተላለፍ አዲስ አይደለም፡፡ ከአሜሪካን ሴንተር ፎረ ዲዚዝ ኮንትሮል ኤንድ ፕሬቨንሽን በተገኘ መረጃ መሰረት በሰዎች ከሚከሰቱት አዳዲስ በሽታዎች ወስጥ ከአራቱ ሦስቱ የሚመጡት ከእንስሳት ነው፡፡ በሽታዎቹ ከእንስሳት ወደ ሰው ሲተላለፉ ከባድ ይሆናሉ፣ ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

ባሃት ኪሮ የእንስሳት በሽታ ባለሙያ ነው፡፡ አቶ ኪሮ ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡- “በእንስሳት በኩል ወደሰው የሚመጡ በሽታዎች ዞኦኖሲዝ ይባላሉ፡፡  ይህን ለመከላከል ነው ዛሬ እዚህ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንኳን የዱር ስጋን በጣም የምንከለክለው፡፡ የሰው ልጅ ብዝሃ ሕይወት ላይ የሚፈጥረው ጫና ችግር እየፈጠረ ነው፡፡”

በዚህ አካባቢ እንጨት ለመቁረጥ፣ መሬት ለማረስ እና የዱር እንስሳትም ለማደን ሲሉ ያካባቢው ሕዝብ  እንደ ቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ የመሳሰሉ ጥብቅ ቦታዎችን እየተጋፉ ነው፡፡ ከሰል ማክሰል እያደገ ያለ ሥራ ነው፣ ባካባቢውም በቂ የእርሻ መሬት የለም፣ አንስሳትም ለምግብነት እና ለንግድ ያገለግላሉ፡፡ እነዚህ እንቅስቀሴዎች በአካባቢው ባሉ የታጠቁ ቡድኖች ድጋፍ ይከናወናሉ፡፡

የኮሮናቫይረስ አለምአቀፍ ወረርሽኝ ምንጩ እና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍበት ትክክለኛው መንገድ ገና የሚጣራ ጉዳይ ቢሆንም ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው እንደተላለፈ ግንዛቤ አለ፡፡

ነገር ግን ስጋ – በተለይም የዱር ስጋ – ገምቢ ምግብ ለማግኘት ብቸኛው መንገድ አይደለም፡፡ ባንቱ ሉካምቦ በምስራቃዊ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የአካባቢ ጥበቃ እና ዘላቂ ልማት ላይ የሚሠራ አገር በቀል ድርጅት አስተባባሪ ነው፡፡ የየሰዉ ገምቢ ምግብ ፍላጎት የተለያየ ሲሆን ምክንያቱ የሰውነታቸውን ክብደት ጨምሮ ሌሎችም መስፈርቶች አሉ ይላል፡፡ “ገምቢ ምግብ ልክ ከእንስሳት እንደምናገኘው ሁሉ ከእጽዋትም ማግኘት እንችላለን፡፡ የሰው ልጅ አካል ሁሉንም [ዓይነት] ገምቢ ምግቦች ይፈልጋል” ይላል አቶ ሉኮምቦ፡፡

ሕገ ወጥ አደንን እና የዱር ሥጋ ምግብነትን ለመቀነስ የሱ ድርጅት በቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ ዙርያ ያሉ አርሶ አደሮችን እንጉዳይ ምርት ለማስለመድ የማሕበረሰብ የእንጉዳይ ማፍያ ቦታዎች እና እና የእንጉዳይ እርሻ አቋቁሟል፡፡

ይህ ጽሁፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡