- Barza Wire - https://wire.farmradio.fm -

ናይጄሪያ፡- በኮቪድ-19 እግድ የተነሳ አርሶ አደሮች የግብርና ግብኣቶችን ለማግኘት እየተቸገሩ ነው

ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ነው፤ ቤሎ ኢሊያሱ በኮቪድ-19 ምክንያት የሕዝብ ትራንስፖርት ስለታገደ ካዱና ግዛት ውስጥ ወዳለው እርሻው በሞተር ሳይክል እየሄደ ነው፡፡ ከቤቱ 17ኪሜ ርቆ ወደሚገኘው እርሻው የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም አይችልም፡፡

“መንገዱ ጥሩ ከሆነ ለመድረስ አንድ ሰዓት ያክል ይወስድብኛል፡፡ አውቶብሶቹ ባብዛኛው አቁመዋል፣ አልፎ አልፎ ብቻ ነው የሚጓዙት፡፡”

ቤሎ በቆሎ፣ አኩሪ አተር እና እሩዝ የሚያመርት አነስተኛ አርሶ አደር ነው፡፡ በናይጄርያ ሰሜናዊ ምእራብ ክፍል በካዱና ግዛት ይኖራል፡፡ ከመጋቢት ጀምሮ የናይጄርያ መንግስት አካላዊ እርቀት እና እንቅስቃሴ እግድ ሲያውጅ የግብርና ግብኣቶችን ለማግኘት ከተቸገሩት አርሶ አደሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

በኮቪድ-19 በተደረገው የእንቅስቃሴ መወሰን የተነሳ ዘር እና ማዳበርያ ለማግኘት እንደተቸገር ይናገራል፡፡ በተጨማሪም የግብርና ግብኣቶች ዋጋም አሻቅቧል፡፡

የናይጄሪያ መንግስት የኮቪድ-19 መከላከያ እርምጃዎችን ከመውሰዱ በፊት አርሶ አደሮች ዘር፣ ማዳበርያ እና ሌሎችንም ግብኣቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ያገኙ እንደነበር ይናገራል፡፡ ቤሎ ጨምሮም እንዲህ ይላል፡- “አሁን ግን ሁኔታው በጣም ተቀይሯል፡፡ የበቆሎ ዘር ዋጋ ከ140 ወደ 140 ናይራ (ከ0.36 ወደ 0.41 ዶላር) በኪሎ ጨምሯል፣ አንድ ከረጢት ማዳበርያ ደግሞ ከ6,500 ወደ 8,200 ናይራ (ከ17 ወደ 21 ዶላር) ጨምሯል፡፡”

የኮቪድ-19 እገዳዎች እየላሉ ቢሆንም ብዙ አርሶ አደሮች ግን የግብርና ግብኣት ባስፈለጋቸው ጊዜ ወጭው ቆንጠጥ እያደረጋቸው ነው፡፡

ስቴላ ጆን-ጃክ ሌጎስ ከተማ አጠገብ ኦጉን ግዛት ውስጥ አርሶ አደር ናት፡፡ በዋጋ መጨመር ምክንያት የግብርና ግብኣቶች ለመግዛት እየተቸገረች ነው፡፡ ስታብራራም እንዲህ ትላለች፡- “ካሳቫ፣ በቆሎ፣ ኮኮያም እና ቆስጣ አመርታለሁ፤ ችግሩ ግን የዘር ዋጋ እጥፍ ጨምሯል፡፡ ለምሳሌ ከእግዱ በፊት የበቆሎ ዘር 20,000 ናይራ (52 ዶላር) እንገዛ ነበር፡፡ አሁን ግን 40,000 ናይራ (103 ዶላር) ደርሷል፡፡”

ስቴላ ጨምራም እንዲህ ትላለች፡- “በዚህ አመት ትርፌ ይቀንሳል፣ በዚህ አመት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገባውን ልጄን እንዴት እንደምግፍ አላውቅም፡፡ አገር አቋራጭ ትራንስፖርት በመንግስት በመታገዱ እና ኦጉን ውስጥም ከፍተኛ የትራንስፖርት እግድ በመኖሩ የግብኣት እጥረት ይፈጠራል ያሉ ነጋዴዎች ዋጋ ጨምረዋል፡፡”    

ቢትሩስ ሉካ በሰሜን ማእከላዊ ናይጄርያ በፕላቶ ግዛት ውስጥ አርሶ አደር ነው፡፡ በቆሎ፣ ድንች፣ ለውዝ እና አኩሪ አተር ያመርታል፡፡ በእንቅስቃሴ እግድ እርምጃዎች ምክንያት የማዳበርያ ዋጋ እንደጨመረ ይናገራል፡፡

ቢትሩስ እንዲህ ይላል፡- “መንግስት አንድ ከረጢት ማዳበርያ በ5,500 ናይራ (14 ዶላር) መሸጥ አለበት ብሏል፣ ሰዎች ግን ገበያ ላይ 8,000 ናይራ (21 ዶላር) እየሸጡት ነው፡፡ ዩርያ ማዳበርያ ልግዛ ብትል ደግሞ ከዚያ በላይ ነው፡፡”

ዴቪድ ዱንግም በፕላቶ ግዛት ውስጥ አርሶ አደር ነው፤ ዶሮ ያረባል፣ በቆሎም ያመርታል፡፡ እሱ በሚኖርበት ግዛት የእንቅስቃሴ እግዱ ከባድ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሲያብራራም እንዲህ ይላል፡- “መጀመርያ ላይ እግዱ ከመላላቱ በፊት ከፖሊስ ፈቃድ መጠየቅ ያስፈልግ ስለነበር ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ከባድ ነበር፡፡ አንድ ጓደኛየ ያለፈቃድ ወደ እርሻው ለመሄድ ሲሞክር ተይዞ ታስሮ ነበር፡፡”

እንቅስቃሴ በመታገዱ ምክንያት የዶሮ መኖ እና የማዳበርያ ዋጋ ጨምሮ እንደነበር ዴቪድ ይናገራል፡፡ “የዶሮ መኖ በጣም ጨመረ፤ ማዳበርያም ዋጋው 50 በመቶ ስለጨመረ በጣም ውድ ሆኖ ነበር፡፡ የማዳበርያ ዋጋ አስተማማኝ ስላልሆነ መጣ ሲባል ሰዉ ሁሉ ገዝቶ ለማጠራቀም ይሯሯጣል፡፡” 

ሲቀጥልም እንዲህ ይላል፡-“ከእግዱ በፊት አንድ ከረጢት የዶሮ መኖ ለመግዛት 3,250 ናይራ (8.41 ዶላር) እገዛ ነበር፤  አሁን ግን ዋጋው ወደ 3,700 ናይራ (9.57 ዶላር) ጨምሯል፣ አንዳንዴም 4,500 ናይራ (11.64 ዶላር) ይደርሳል፡፡”

የማዳበርያ እጥረት የዘር ጊዜውን በማዘግየቱ ዴቪድ ያሰበውን እንዳይዘራ አድርጎታል፡፡ “ማዳበርያ ቶሎ ስላላገኘሁ እንደ አይሪሽ ድንች ያሉ ልዘራቸው ያሰብኳቸውን ሰብሎች መትከል ሳልችል ቀርቻለሁ፡፡ ይሄ የሆነው በኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ እግድ የተነሳ ነው፡፡ ማዳበርያ በጊዜ መጨመር ስላልቻልኩ የበቆሎ ምርቴም ይቀንስብኛል፡፡”

ለብዙ አርሶ አደሮች በኮቪድ-19 የእግድ እንቅስቃሴዎች የተነሳ አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ወቅት የነበረ ቢሆንም ቤሎ አርሶ አደሮች ጠንክረው መስራት እንዲቀጥሉ እና ለግብኣት አቅርቦት ችግር የፈጠራ መንገዶችን በመጠቀም እርሻቸው ላይ እንዲያተኩሩ ይመክራል፡፡

እንዲህ ይመክራል፡- “ማዳበርያ መግዛት ካልቻላችሁ እንደ ተፈጥሮ ቀልዝ ያሉ አማራጮችን ተጠቀሙ፡፡ የግብርና መሳርያዎችን መከራየት ካልቻላቸሁ ከቤተሰዎቻችሁ ወይም ጎረቤቶቻችሁ ጋር  የእርሻ ሥራችሁ ላይ ተጋገዙ፡፡”

ይህ ጽሑፍ በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡