ቤኒን፡- የሴቶች ማህበራት ሴቶችን በውሳኔ ሰጭነት ለማሳተፍ ይታገላሉ

| December 1, 2020

Download this story

News Brief

በቤኒን ሴቶች አንድ ላይ በመጣመር ሕይወታቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በውሳኔ ሰጭነት እንዲሳተፉ እየጠየቁ ነው፡፡ በቤኒን ሴቶች በውሳኔ ሰጭነት ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡ በሃገሪቱ በምርጫ ስልጣን ከያዙ 1,815 ሰዎች ውስጥ 78ቱ ብቻ ሴቶች ናቸው፡፡ማሪየት ሞንቾ የምእራብ አፍሪካ ወጣት ሴቶች አመራር ጥምረት ፕሬዚደንት ናት፡፡ ወጣቶች እና ሴቶች እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ግጭቶች እና ቀውሶች ዋነኛ ተጠቂዎች ስለሆኑ ጠቃሚ ውሳኔዎች ላይ መሳተፍ አለባቸው ትላለች፡፡ ለዚህ አነስተኛ ውክልና ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ባለሙያወች ይናገራሉ - ከነዚህም ውስጥ “ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፣በሴቶች መካከል ያለው ከፍተኛ መሃይምነት፣ በዋናነት ድህነት ሴቶችን ማጥቃቱ [እና] ዝቅተኛ የሆነው የሴቶች መጎልበት” ይገኙበታል፡፡

መስከረም አጋማሽ ላይ አንድ ቀን ከጥዋቱ አንድ ሰዓት፡፡ የቤኒን ኢኮኖሚያዊ ዋና ከተማ የሆነችው የኮተኑ ሰማይ በማለዳ ጭጋግ ተሸፍኗል፡፡ ጥሩ ያልሆነው የአየር ጸባይ ግን ከበርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመጡ ወጣት ሴቶችን እና አክቲቪስቶችን እና የፖለቲካ ተዋንያንን ወደ ምእራብ አፍሪካ ወጣት ሴቶች መሪዎች ጥምረት ቢሮ ከመምጣት አላገዳቸውም፡፡

ሴቶቹ በምርጫ ወቅት ስለተፈጠረ ግጭት የሚቀርብ ሪፖርትን ለማዳመጥ ነበር የመጡት፡፡ የሴቶቹ ጥምረት መስከረም 11 ቀን የሚከበረውን አለም አቀፍ የሰላም ቀን ለማክበር የሰላም ግንባታ ወር የሚል እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ማሪየት ሞንቾ የጥምረቱ ፕሬዚደንት ናት፡፡ “በግጭት ጊዜ ወጣቶች እና ሴቶች ዋነኛዎች ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነሱን ማሳተፍ እና ማስተማር አስፈላጊ ነው” ትላለች፡፡

ቤኒን ውስጥ ሴቶች በተለይ በቀውስ ወቅት ከውሳኔ ሰጭ ሂደቶች እና አካሎች ይገለላሉ፡፡ ሴቶች 12 ሚሊዮን ከሚሆነው የቤኒን ሕዝብ ውስጥ 50.7% ይሸፍናሉ፡፡ ነገር ግን በሃገሪቱ ውስጥ በምርጫ ስልጣን ከያዙት 1,815 ሰዎች ውስጥ 78ቱ ብቻ ሴቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስት 31 የከተማ ምክርቤት አባላት ናቸው፡፡ ከ24ቱ የመንግስት ሚኒስትሮች ውስጥ አምስቱ ብቻ ሴቶች ናቸው፡፡ ከ83ቱ የፓርላማ አባላት ውስጥ ስምነቱ ብቻ ሴቶች ናቸው፡፡

ፍራንስዋዝ አግባዎሉ ሴቶች በአፍሪካ ሕግ እና ልማት የተባለ መያድ አስተባባሪ ናት፡፡ “የሴቶች ውክልና ማነስ እና በውሳኔ ሰጭ አካላት ውስጥ የመሳተፍ ጥያቄ የመጣው ከማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጥረቶች፣ መሃይምነት በሴቶች ከመብዛቱ፣ ድህነት በዋናነት ሴቶችን ከማጥቃቱ፣ ሴቶችን ማጎልበት ዝቅተኛ ከመሆኑ፣ ሴቶች የፖለቲካ ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ እና ፍላጎት የሚያሳዩት ደግሞ ከሚሰጣቸው ቦታ ጋር ከተያያዙ ችግሮች ነው” በማለት ታብራራለች፡፡

በውሳኔ ሰጪ አካላት ውስጥ ተጨማሪ ሴቶች እንዲሳተፉ የሚደረገው ጥረት አካል የሆነውን የእኩልነት ሕግ ቤኒን በ2019 አሳልፋለች፣ ለመፈጸም ግን እየታገለች ነው፡፡

ወይዘሮ ሞንትቾ እንደምትናገረው የሷ የሴት አመራሮች ጥምረት በማንኛውም የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት አልተሳተፈም፣ አካላዊ እርቀትን እና ገበያ መዝጋትን የመሳሰሉ እርምጃዎችም ሲወሰዱ ሃሳብ አልተጠየቀም፡፡ ሌሎች ማህበራት እና ጥመረቶችም በውሳኔ አሰጣጡ ሂደት ባለመሳተፋቸው አማርረዋል፡፡

በምእራብ አፍሪካ ሴቶች በኢመደበኛ ዘርፍ አስተማማኝ ያልሆኑ ሥራዎች ስላሏቸው የጤና ቀውሶች ሲፈጠሩ የመጀመርያዎቹ ገፈት ቀማሾች እነሱ ናቸው፡፡ ገቢ እንዲያጡ በማድረግ ወረርሽኙ የሴቶችን ጉዳት ተጋላጭነት ከፍ አድርጓል፡፡ የሴቶች የምግብ ዋስትና ቀንሷል፤ ጾታ ተኮር ጥቃቶችም ጨምረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሴቶች ስለጤና ቀውሱ በቂ መረጃ አያገኙም፤ እንደ ጤና እና ትምህርት ያሉ መሰረታዊ ማሕበራዊ አገልግሎቶችም ለሴቶች ተደራሽነታቸው ውስን ነው፡፡ እኒዘህ ምክንያቶች በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት የበለጠ አስፍተውታል፡፡

ኮቪድ-19 በቤኒን ያስከተለውን ቀውስ ተከትሎ መንግስት ከቤት ውጭ ማስክ መልበስን አስገዳጅ በማድረግ፤ የውሃ ዳርቻ መዝናኛዎችን፣ የአምልኮ ቦታዎችን እና መጠጥ ቤቶችን መዝጋት የመሳሰሉ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በደቡባዊ ቤኒን በሚገኙ አስር ለጉዳት የተጋለጡ የከተማ አስተዳደሮችም እንቅስቃሴ በሚገድብ “በሕዝብ ጤና አጥር” እንዲከበቡ አድርጓል፣ የህዝብ ማጓጓዣ መኪኖችም እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል፡፡

እነዚህን እርምጃዎች ለማዘጋጀት እና ለመተግበር ሊማከሩ የሚገባቸው ብዙ የሴቶች ድርጅቶች እና ጥምረቶች ነበሩ፡፡ ወይዘሮ ሞንትቾ እንደሚናገሩት “የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች በቅንጅት አይሠሩም፡፡ … ተመሳሳይ ሃላፊነቶች፣ ተመሳሳይ አላማ እና ኢላማ ያላቸው ነገር ግን ተነጣጥለው የሚሠሩ ማሕበራት አሉ፡፡ የሲቪል ሶሳይቲ ማሕበራት ሚናቸውን ለመጫዎት እና ሃላፊነት ለመውሰድ ሃላፊነቱ የነሱ ነው፡፡”

ኬር የተባለው ዓለም አቀፍ መያድ ቤኒን ውስጥ የሚሠራ ሲሆን ሴቶችን ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ለማሳተፍ ይሞክራል፡፡ አኩዌሊን ቤሃንዚን ዶሴ የኬር ፕሮግራም አስተባባሪ ናት፡፡ “ሴቶች በአካባቢያቸው የምክክር ማዕቀፍ ውስጥ እንዲወከሉ ማድረግ አለብን” ትላለች፡፡

ወይዘሪት ዶሴ ባለስልጣናቱ በአካባቢያቸው የሚገኙ የሴቶች ቡድኖችን ያውቃሉ ትላለች፡፡ የእነዚህ የሴቶች ቡድኖች አመራሮች በአካባቢያቸው፣ በከተማ መስተዳድሮች፣ በዲፓርትመንቶች እና በሃገር አቀፍ ደረጃ የምክክር ማእቀፍ ውስጥ እንዲካተቱ መደረግ አለባቸው ትላለች፡፡ በሜዲያ እና ተሰሚነት ባላቸው ሰዎች አማካኝነት የማነቃቃት እና የተግባቦት ሂደት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ትናገራለች፡፡

የሴቶች ማህበራት እና ጥምረቶች ሴቶች በሚገባ በቤኒን ውሳኔ ሰጭ አካላት ውስጥ እንዲካተቱ ጥረት ማድረግ ለመቀጠል አቅደዋል፡፡

ይህ ጽሑፍ በግሎባል አፌይርስ በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡

ፎቶ:- ቤኒን ውስጥ ያሉ የሴቶች የመንደር ቁጠባ እና ብድር ቡድን