Ethiopia: Farmers tend sorghum with care (Amharic)

| January 15, 2018

Download this story

ማሽላ በወሎ ዞኖች ዋነኛ ምርት ነው፡፡ የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ በርግጥ ይህ አካባቢ የማሽላ መቀነት ተብሎ ይታወቃል፡፡ የማሽላ ምርት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም በጣም ምቹ ነው፡፡

መሓመድ አሊ ይባላል፡፡ በቃሉ ወረዳ ጠረፎ መንደር ነዋሪ ነው፡፡ ስድስት ልጆች – አራት ወንድና ሁለት ሴት ልጆች አሉት፡፡ ቄዬው ስንደርስ ማሽላ እያረመ አገኘነው፡፡ መሓመድም ማሽላ ከልጅነቱ ጀምሮ ዋነኛ ምርታቸው እንደሆነና በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰ መሆኑን ይናገራል፡፡

በማሽላ የምርት ሂደት ውስጥ የመሬት ዝግጅት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን መሓመድ ገልጾልናል፡፡ ከመጀመሪያው እርሻ ጀምሮ ወቅቱን ጠብቆ ማረስ ዘሩን በጊዜ ለመዝራት ይረዳል ይላል መሓመድ፡፡ “የመሬት ዝግጅት ማሽላ ምርት ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ በጊዜ ካልታረሰ የመዝሪያ ወቅት ሊያመልጥ ይችላል፡፡ ይህ ዝናብ ቢዘንብም ባይዘንብም ይከናወናል፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያው በጊዜና በትኩረት እሰራለሁ፡፡”

የመጀመሪያ እርሻ የማሽላ አገዳን በመንቀል ከማሳ ውስጥ ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ባለሙያዎች ምክር መሰረት የማሽላ አገዳን ከማሳ ውስጥ ማፅዳት የማሽላ አገዳ ቆርቁር ቁጥርን በእጅጉ ስለሚቀንስ ለቀጣይ ምርት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይናገራል፡፡ የፀረ-አገዳ ቆርቁር ኬሚካልም ይጠቀማል፡፡

መሓመድና በአከባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ጠንገላይ የተሰኘውን የማሽላ ዝርያ ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ዝርያ ቶሎ የሚደርስ የዘር ዓይነት ነው፡፡ ከተለመዱ የማሽላ ዝርያዎችም የተሻለ ምርት ይሰጣሉ፡፡ የዝናብ እጥረት በአፈር ውስጥ የእርጥበት መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ “አካባቢያችን ከሌሎች ቦታዎች አንፃር ሲታይ አነስተኛ ዝናብ ነው፡፡ በመሆኑም ቶሎ የሚደርሱ ዝርያዎችን መጠቀም በዝናብ እጥረት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ይረዳል” ይላል መሓመድ፡፡

መሓመድ ከዚህ በተጨማሪ ምርቱ በእርጥበት እጥረት እንዳይጎዳው በእርጥበት እቀባ ዘዴ ይቋቋማል፡፡ በማሳው ዙሪያ ቦይ በማበጀት ውሃውን በማሳው ዙሪያ በማከማቸትና በየመስመሮቹ መሃል ባሉት ቦዮች በማሰራጨት ሰብሉ እርጥበት እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ቦዮቹን ቀደም ብሎ ነው የሚያዘጋጀው፡፡

መሓመድ ለበርካታ ዓመታት በተለምዶ በሚዘራበት ወቅት በእውቀት ማነስ የተነሳ በጣም ትንሽ ምርት ነበር የሚያገኘው፡፡ “ከአንድ ጥማድ መሬት አምስት ወይም ስድስት ኩንታል ነበር የምናመርተው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በባለሙያዎች ድጋፍ በምናገኘው መረጃ ግንዛቤያችን በመዳበሩ አሁን እጥፍና ከዚያ በላይ ምርት እናገኛለን፡፡”

ወ/ሮ ሰንደል አህመድ በተረፎ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ እርሳቻውም ለበርካታ ዓመታት ማሽላን የማምረት ልምድ አላቸው፡፡ የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሰንደል የማሽላ አገዳ ቆርቁርን ለመከላከል በአብዛኛው አገዳውን በፀሐይ አስጥቶ ከማሳ ላይ ሙልጭ አድርገው ያስወግዳሉ፡፡ ቁርቁራ የሚባል ጉቶ በተለይ የአገዳ ቆርቁር መጠለያ ስለሚሆን እሱንም ከማሳ ውስጥ ያፀዳሉ፡፡ ኬሚካልም በመርጨት ይከላከላሉ፡፡
ወ/ሮ ሰንደል ከዚህ ሌላ የመከላከያ መንገድም አላቸው፡፡ ብዙም ወጪ ሳያስወጣቸው በልማዳዊ መንገድ የከብቶችን ሽንት ለሁለት ሳምንታት ከድነው በማስቀመጥና ማሽላው ላይ በመርጨት ይከላከላሉ፡፡ የተጎዳ አገዳ ደግሞ ነቅለው ያስወግዳሉ፡፡

“አዝመራ ችግር የለብንም፡፡ በደንብ ስለምንንከባከብ ጥሩ ምርት እናገኛለን፡፡ አሁን እህል ተወዷል፡፡ አንድ ጭነት 600 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የተረጋጋ ገቢ ስለነበረኝ በግብር ወቅትና በርካሽ ጊዜ ባለመሸጤ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ይኸን ማድረግ የቻልኩት ደግሞ በቂ ምርት ማምረት በመቻለ ነው” ይላሉ ወ/ሮ ሰንደል፡፡

አቶ ጌታቸው ወ/አረጋይ የቃሉ ወረዳው ሰብል ልማት በለሙያ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደነገሩን ማሽላ በሚመረትበት ወቅት የዝናብ እጥረትና የዘር አብዝቶ መዝራት ችግሮችን ለመቋቋም በተከታታይ ዓመታት ከተወሰደው እርምጃዎች አንዱ በመስመር መዝራት ነው፡፡ “ፓኬጁ በሚያዘው መሰረት በመስመር መካከል 75 ሳ.ሜ በተክል መካከል ደግሞ 20 ሳ.ሜ ርቀት አንዲኖር ተደርጎ እንዲዘራ እንመክራለን” ይላሉ አቶ ጌታቸው፡፡ አርሶ አደሮችን እየተገበሩት እንደሚገኝና ይህ አዘራር ደግሞ ለእርጥበት እቀባ ስራ አጋዥ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡”

እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ የማሳ አናት ትሬንች መስራትም ዝናብ መዝነብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጎርፍ ምክንያት የሚመጣውን ውሃ ማሳ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በማሳ አናት ላይ በማቆር እርጥበት እንዲከማች ያደርጋል፡፡ ይህ የአካባቢውን የውሃ መጠን ለመጨመር ያስችላል፡፡

ሌላው ከመሬት ዝግጅት ወቅት ጀምሮ በማሳ ውስጥ በየሁለት ወይም ሶስት ሜትሮች ርቀት እንደ አፈሩ ዓይነት በባለሙያዎች እገዛ ቦይ እየታሰረ ማሳ ውስጥ የገባውን ውሃ እንዲከማች ማድረግ ነው፡፡ በእርሻ ወቅት ይህን ያልሰሩ አርሶ አደሮች ካሉ በአካፋ እየቀደዱ መስመሩን ማበጀት ይችላሉ፡፡ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ አርሶ አደሮቹ በማሳ ውስጥ በመገኘት እንደየውሃው መጠን መስመሩን እንዲዘጉና እዲከፍቱ ይመክራሉ፡፡

ይህ ጽሁፍ በቢል አና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ስቴፕልስ ፕሮጄክት ድጋፍ የተዘጋጀ ነው